ግብረ ኃይሉ የስቅለት እና የትንሳዔ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ።

89
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
በዓላት ሲቃረቡ ከወትሮው የተለየ የእግረኞች እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ይስተዋላል፤ ይህንን እንቅስቃሴ ተከትሎ በተለያዩ ስፍራዎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እና የትራፊክ አደጋ እንዳያጋጥም የፀጥታ ተቋማት ሙሉ የሰው ሃይላቸውን በሥራ ላይ በማሰማራት ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩበት ወቅት ነው፡፡
በዘንድሮው የስቅለት እና የትንሳዔ በዓላት ወቅትም ሆነ ከበዓላቱ አስቀድሞ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በተለይም በገበያ ስፍራዎች፣ በመዝናኛ ቦታዎች እና በዕምነት ተቋማት አካባቢ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የፀጥታ ድባብ እንዲኖር የሚጠበቅበትን ኅላፊነት ለመወጣት የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡
የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እና የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ እንዳያጋጥም የትራፊክ ፖሊሶችና ሌሎች የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚያከናውኑትን ተግባር ኅብረተሰቡ ሊደግፈው እንደሚገባ የጠቀሰው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል፤ ጠጥቶ ባለማሽከርከር፣ የዕርድ እንስሳትን በተሽከርካሪ መንገድ ላይ ባለመንዳት እንዲሁም ተገቢውን የትራፊክ ደንብ አክብሮ በመጓዝና ለትራፊክ ፍሰት እንቅፋት ከሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ራስን በማራቅ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብሏል፡፡
በገበያ ቦታዎች ፣ በትራንስፖርት መጠበቂያ ስፍራዎች እና ሌሎች የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ግርግሩን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እንደሚኖሩ በመገንዘብ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ የመከላከል ሥራውን በትኩረት እንደሚያከናውን ገልፆ ኅብረተሰቡም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡
በዓሉ የሰላምና የደስታ በዓል ሆኖ እንዲያልፍ እና የዕምነቱ ተከታዮች ያለምንም የፀጥታ ሥጋት ያከብሩ ዘንድ በዚህ የፀጥታ ማስከበር ሂደት ውስጥ በአካባቢያቸው ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከቱ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ግብረ ኃይሉ ጥሪ አስተላልፏል።
በመጨረሻም በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆን ምኞቱን ገልጿል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ቀንም አልነበረም፣ ሌሊትም አይደለም”
Next article“የአማራ ልዩ ኀይል ክብሩን በሚመጥን፣ መብትና ጥቅሙንም በሚያረጋግጥ መልኩ ነው ተመልሶ የሚደራጀው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ