“የአማራ ልዩ ኀይል ክብሩን በሚመጥን፣ መብትና ጥቅሙንም በሚያረጋግጥ መልኩ ነው ተመልሶ የሚደራጀው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

443
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በተለያዩ የክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። የክልሉ ልዩ ኀይል አባላትን መልሶ ስለማቋቋም ሂደት፣ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ እና ስለክልሉ ወቅታዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች አንስተዋል።
አቶ ግዛቸው የክልል ልዩ ኀይሎችን መልሶ የማደራጀት ሂደቱን ሌላ መልክ እና እሳቤ በመስጠት የጸጥታ ችግር ለመፍጠር የፈለጉ አካላት በሚዲያ ጭምር ታግዘው ሲሠሩ ነበር ብለዋል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በዚሁ የተዛባ መረጃ ሰበብ እንደነበርም ተናግረዋል።
አቶ ግዛቸው መንግሥት የክልሉን እና የሕዝቡን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ውሳኔ ውስጥ ሊገባ እንደማይችል መታመን አለበት ነው ያሉት። በመኾኑም በመንግሥት እና ሕዝብ መካከል አለመተማመን በመፍጠር አላስፈላጊ የፖለቲካ ትርፍ የሚሹ አካላትን በጋራ መከላከል ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልል ልዩ ኀይሎች ወደ ፌዴራል የጸጥታ ተቋማት እንዲካተቱ እንጅ እንዲበተኑ እንደማይደረግም ገልጸዋል። የአማራ ልዩ ኀይል አባላትም በመረጡት ተቋም እንዲቀላቀሉ እና የተሻለ ተልዕኮ እንዲወስዱ ይደረጋል ነው ያሉት።
“የልዩ ኀይል አባላትን መልሶ በማደራጀት ሂደቱ የሚደናገር አካል መኖር የለበትም” ያሉት አቶ ግዛቸው በውሳኔው ላይ መተማመን እንዲፈጠር ለልዩ ኀይል አባላት እና ለመላው ሕዝብ ግልጽ የማድረግ እና የመረዳዳት ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
“ውዥንብር ለመፍጠር በሚወራው መልኩ ሳይኾን የአማራ ልዩ ኀይል ክብሩን በሚመጥን፤ መብትና ጥቅሙንም በሚያረጋግጥ መልኩ ነው የሚደራጀው” ሲሉም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።
በተፈጠረው መደናገር ወጣቶች ስሜታቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ ወጥተው እንደነበር የገለጹት ቢሮ ኀላፊው ሂደቱ በሰከነ እና በሰለጠነ መልኩ መኾኑ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
አቶ ግዛቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበርም ገልጸዋል። ወቅቱ የበዓል ሰሞን በመኾኑ ተጓዦችን ያጉላላ እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና የፈጠረ ስለመኾኑም ተናግረዋል። አሁን ላይ ሰላማዊ የሕዝብ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ እና የትራንስፖርት አገልግሎቱም በመደበኛ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል አለመተማመንን በመፍጠር የጸጥታ ችግር እንዲከሰት የሚጥሩ አካላት ስለመኖራቸውም አንስተዋል። እንደ አቶ ግዛቸው ገለጻ የነዚህ አካላት ዋነኛ አጀንዳ ሕዝቡን እረፍት በመንሳት ልማት እንዲቋረጥ እና ወደ አልባሌ ቀውስ እንዲገባ ታሳቢ ያደረገ ነው። ተገቢ እና የታወቀ ምንጭ ያላቸውን መረጃዎች በመቀበል ከአላስፈላጊ ውዥንብር ራስን መጠበቅ እንደሚያስፈልግም መልእክት አስተላልፈዋል።
አቶ ግዛቸው የአማራ ክልል ችግሮቹን የመፍታት አቅሙ የበለጠ እንዲጎለብት ለማስቻል በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም በመግለጫቸው አንስተዋል።
ይህ ወቅት ለመኸር እርሻ ግብዓት የሚቀርብበት በመኾኑ የክልሉ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራበት ነው ብለዋል። አርሶ አደሮችም ከምንጊዜውም በላይ ጠንክረው በመሥራት ራሳቸውን ብሎም ሀገርን የተሻለ ኢኮኖሚ ባለቤት ማድረግ እንዲችሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
የክልሉ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ፍሰትም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ እየጨመረ ስለመምጣቱ አቶ ግዛቸው ገልጸዋል። የቱሪስት መዳረሻዎችን የበለጠ በማስፋት ዘርፉን የኢኮኖሚ ምንጭ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ለኢንቨስተሮች ተገቢ አገልግሎት በመስጠት ለወጣቶች የሥራ እድል አማራጮችን ለማስፋትም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleግብረ ኃይሉ የስቅለት እና የትንሳዔ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ።
Next article“በገና ትልቅ የጥሞና፣ የጸሎትና የምስጋና መንፈሳዊ መሳሪያ ነው”