
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ሀገረ ስብክት ገዳመ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር እና የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር ዘላለም በላይ ስለ ነገረ ስቅለቱ ሲያብራሩ ፀሐይ ጨለመች፣ ጨረቃ ደም ለበሰች፣ ምድር ተጨነቀች፡፡ ምድራዊያን ፈጣሪያቸውን ሰቀሉት፣ ምድራዊያን አዳኛቸውን አንገላቱት፣ ምድራውያን አምላካቸውን ቸነከሩት፣ ቅዱስ ደሙን አፈሰሱት፣ ቅዱስ ስጋውን ቆረሱት፡፡
ሁሉም ያለው ጌታ ስለ ፍቅር ተንገላታ፣ በጥፊ ተመታ፡፡ ፍቅሩም ደም በማፍሰስ፣ ስጋ በመቁረስ የተገለጸ ዘላለማዊ ፍቅር ነበር፡፡ የሕይወት እንጀራ የሚሰጠውን እና የሕይወት ውኃ የሚያጠጣውን መራራ ሐሞት አስጎነጩት፣ መላዕክት የሚያመሰግኑትን፣ ክንፋቸውን እያማቱ የሚያገለግሉትን አሰቃዩት፡፡
ሁሉም የሚቻለው፣ በሁሉም ሥፍራ ያለው፣ ሁሉንም የሚያውቀው አምላክ ስለ ፍቅር መከራን ተቀበለ፡፡ ተበዳይ ሳለ ካሰ፣ ቅዱስ ስጋውን ቆረሰ፣ ክቡር ደሙን አፈሰሰ፡፡ ደግ ነው ስለ ሰዎች ሐጢያት እርሱ ተሰቃየ፡፡ ያለ በደሉ እንደ በዳይ ተቆጥሮ ተገፋ፣ ተዳፋ ሲሉ ያብራራሉ መምህሩ፡፡
የበደለውን የሰውን ልጅ ለማዳን ከሰማያት የወረደው፣ ከድንግል ማርያም በድንግልና የተወለደው ክርስቶስ የሚሰቀልበት ጊዜው ደርሶ ነበር፡፡ ጊዜው በደረሰም ጊዜ በአስቆሮቱ ይሁዳ እጅ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ የአይሁድ ጭፍሮችም ያዙት፡፡ በያዙትም ጊዜ አሰቃዩት፡፡
የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህሩ ዘላለም በላይ እንደነገሩን ክርስቶስን ሊይዙት በመጡ ጊዜ፣ ሾተል፣ መብራት፣ ጎመድ ይዘው ነበር፤ ወደ እርሱ በመጡም ጊዜ ማንን ትፈልጋላችሁ? አላቸው ወደ ኋላ ወደቁ፡፡ ፈረሶቻቸው ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፡፡ ድጋሜ ተነስተው ለመያዝ በፈለጉ ጊዜ ማንን ትፈልጋላችሁ አላቸው? ይህን ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ ወደቁ፡፡
እርሱን ያለ ፈቃዱ መያዝ አይቻልምና፡፡ ኢየሱስ ግን ለአዳም የገባው ቃል ይፈጸም ዘንድ እንዲይዙት ፈቀደላቸው፡፡ ኢየሱስን የያዙት ሰዎችም ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፡፡ ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና በጥፊ የመታህ ማነው ? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር፡፡ ብዙ እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር፡፡ ሌሊቱም አለፈ፡፡ በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰባስበው ወደ ሸንጓቸው ወሰዱትና ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት፡፡ እርሱ ግን ብነግራችሁ አታምኑም፣ ብጠይቅም አትመልሱልኝም ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል አላቸው፡፡ ሁሉን የያዘውን ያዙት፣ ሁሉንም የሚገዛውን አሠሩት፣ በቁጣ ጎተቱት፣ መከራ አበዙበት፣ በፍቅር ተከተላቸው፡፡
ሁላቸውም እንግዲያውስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት፡፡ እርሱም እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው፡፡ እነርሱም ራሳችን ሲናገር ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ፡፡ ወደ ጲላጦስም ወሰዱት፡፡ ጲላጦስም በኢየሱስ ላይ ለፍርድ የሚያበቃ አንዳችም በደል አጣበት፡፡ ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ። በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ። እነርሱ ግን አጽንተው ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል አሉ። ጲላጦስ ግን ገሊላ ሲሉ በሰማ ጊዜ የገሊላ ሰው ነውን? ብሎ ጠየቀ፡፡ ከሄሮድስም ግዛት እንደሆነ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ላከው ፤ እርሱ ደግሞ በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበረና። ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፡፡ ምልክትም ሲያደርግ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን አንድ ስንኳ አልመለሰለትም። የካህናት አለቆችና ጻፎችም አጽንተው እየከሰሱት ቆመው ነበር። ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው ዘበተበትም፡፡ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ላከው። ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን እርስ በርሳቸው ወዳጆች ሆኑ፡፡ ቀድሞ በመካከላቸው ጥል ነበረና።
ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም። ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘበትም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም አላቸው ጲላጦስ፡፡ እነርሱ ግን ኢየሱስን ስቀለው በርባንን ፍታልን አሉት፡፡
ጲላጦስም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚህ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት፡፡ የጲላጦስ ሚስት በዚህ ንፁሕ ሰው ደም ተጠያቂ እንዳትሆን የሚል መልዕክት ከአየችው ሕልም ጋር አብራ በላከችበት ጊዜ ጲላጦስ ጨነቀው፡፡ በአንድ በኩል ኢየሱስን ይቀጣላቸው ዘንድ የሚጠይቁት ጭፍሮች ጩኸት፣ በሌላ በኩል የሚስቱ መልዕክት አስጨነቀው፣ አስጠበበው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን መረመረው አንዳችም በደል አላገኘበትም፡፡ እኔ ከዚህ ንፁሕ ሰው ደም ንፁሕ ነኝ ሲል እጁን ታጥቦ ኢየሱስን ሰጣቸው፡፡
መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት፡፡ አነገስንህ እያሉ ሲዘባበቱበት ልብሱን አውልቀው ቀይ ግምጃ አለበሱት፡፡ ከፊት ያለው ወደኋላ ይገፋዋል፣ ከኋላም ያለው ወደፊት ይገፋዋል፡፡ ይገፉታል፣ ያዳፉታል፤ ከፊት ከኋላ እየገፉት፣ ፈረስ እየረገጠው፣ አይሁዳውያን እየረገጡት እየመቱት፣ እየወደቀ እየተነሳ ወደ ቀራንዮ ሄደ፡፡
እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የልጇን መያዝ በሰማች ጊዜ እያለቀሰች፣ እንባ በጉንጮቿ እያፈሰሰች ወደ ቀራንዮ ገሰገሰች፣ አትስቀሉት፣ አትጎትቱት፣ አትቸንክሩት፣ አትግረፉት፣ መራራ ሐሞት አታጠጡት የሚል አልነበረምና ስቃዩን አበዙበት፣ መከራውን አጸኑበት፡፡ እርሷም የልጅዋ የወዳጅዋ መከራ በዝቷልና አብዝታ አለቀሰች፡፡ አንጀቷ በመሪር ሀዘን ተላወሰች፡፡ ያችንም ሀዘን አንደበቶች አይገልጿትም፤ እጅግ የመረረች ናትና፡፡
በቀራንዮ በደረሱም ጊዜ እጅና እግሩን መስቀል ላይ ቸንክረው በቀኝና በግራው በሁለት ወንበዴዎች መካከል ሰቀሉት፡፡ በመስቀል ላይ መከራ አበዙበት፡፡ የሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፉበት፣ በጦር ወጉት፣ ደሙን አፈሰሱት፡፡ በመስቀል ላይ በሰቀሉት ጊዜም ሰዎችን አድናለሁ ትላለህ እስኪ አንተ ውረድ እንይህ ራስህን አድን፣ ደግሞም የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ትላለህ እግዚአብሔር ከወደደህስ ከመስቀሉ ውረድና ዳን እንይህ እያሉ ይዘባበቱበታል፡፡ እርሱም ከመስቀል ወርዶ መዳን ይችል ነበር፡፡ ለአዳም የገባው ቃል ይፈጸም ዘንድ በአይሁድ ሽንገላ ከመስቀል አይወርድምና ዝም አለ፡፡ ምን አይነት መታገስ ነው? ምን አይነት ፍቅር ነው? ምን አይነት መውደድ ነው? ምን አይነት ትሕትና ነው? ምን አይነት ዝምታ ነው?
የማይነካው ተነካ፣ የማይሞተው ሞተ፡፡ እርሱ በተሰቀለ ጊዜ ከዋክብት ረገፉ፡፡ መቃብራት ተከፈቱ፣ አለቶች ተሰነጣጠቁ፣ በብርሃን አስጊጦ የፈጠራት ፀሐይ ጨለመች፣ በብርሃን አስውቦ የፈጠራት ጨረቃ ደም ለበሰች፡፡ የቤተ መቅደስ መጋራጃ ተከፈለ፡፡ ዘጠኝ ሰዓት በሆነም ጊዜ በፈቃዱ ነብሱን ከስጋው ለየ፡፡ በዚያ ጊዜ ቀንም አልነበረም፣ ሌሊትም አልሆነም እለተ አርብ ሁለቱ ነገሮች የተቀላቀሉባት አስጨናቂ ቀን ናትና፡፡ ይላሉ የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህሩ እና የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር ዘላለም በላይ።
ክርስትና ለሰው መኖር ነው ያሉኝ መምህሩ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው ለሰዎች እንደሆነ ሁሉ ክርስቲያኖችም ለሰዎች መኖር አለባቸው ብለዋል፡፡ ለወንድም፣ ለባልንጀራ መታዘዝ፣ ከራስ በላይ ለሌሎች ማሰብ፣ ገደብ የሌለው ፍቅር መስጠት የክርስትና ሕይወት ነው፡፡ ክርስቶስ ተበድሎ እንደካሰ ሁሉ ክርስቲያኖች የበደላቸውን ክሰው፣ የበደላቸውን ፍቅር ሰጥተው ይቅር ይሉ ዘንድ ግድ ይላቸዋል ነው ያሉኝ፡፡
ያቺ ቀን እና ሌሊት የተቀላቀለባት፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የዋለባት፣ ቀንም ያልነበረች፣ ሌሊትም ያልነበረች ጊዜ ዕለተ አርብ ዛሬ ናት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!