ክልሉ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለሱን የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር ገለጹ።

209
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 5/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰላምና ደኅንነት፣ በመልሶ ማቋቋምና በጸረሙስና ሥራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከክልሉ ሰላምና ደኅንነት ጋር በተያያዘ ባነሱት ሀሳብም ሕዝቡ ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣል ብለዋል።
በተለይም ግጭቱ እንዲባባስ የሚፈልጉ አካላት በየጊዜው የሚፈጠር ችግርን በማኅበራዊ ሚዲያ አግዝፎ በማሳየት ለሌላ ችግር የሚዳርጉ ናቸው ብለዋል።
የሰሞኑን የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ተግባር በአማራ ክልል ላይ ብቻ የሚተገበር በማስመሰል እና ተደማሪ ችግር በክልሉ ላይ እንዲፈጠር፣ የሰላም እጦት እንዲከሰት ሠርተዋል ነው ያሉት።
ከሰሞኑ የተፈጠረው ችግር በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መንገድ እንዲዘጋ፣ ግጭት እንዲፈጠርና ሰላም እንዲታወክ የተንቀሳቀሱት ከበስተጀርባ ግጭት አትራፊ አካላት የፈጠሩት ነው ብለዋል።
በእንደዚህ አይነት ብጥብጥ የበለጠ የሚጎዳው ክልሉን ነው ያሉት ዶክተር ጌታቸው፤ ስጋቶችንም ኾነ ችግሮችን በሰከነ ውይይትና ምክክር እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በተፈጠረ የሰላም እጦት የሰዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተገትቶ ነበር፤ የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጥም በርካቶችን ለእንግልት ዳርጓል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ክልሉ ወደ ቀደመው ሰላሙ ተመልሷል ያሉት ዶክተር ጌታቸው፤ በቀጣይም ማንኛውም አካል ችግርን በውይይት ለመፍታት በቀናነት እንዲሥራ አደራ ብለዋል።
በሰሜኑ ጦርነት በአማራ ክልል ኢኮኖሚያዊ፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት መድረሱን በቆይታቸው ያነሱት ዶክተር ጌታቸው፤ እስካሁን በተደረገው ጥናት አማራ ክልል በጦርነቱ ከአምስት መቶ ቢሊየን ብር በላይ ውድመት ደርሶበታል ብለዋል።
በክልሉ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባትና መልሶ ለማቋቋም ጽሕፈት ቤት በማቋቋም እየተሠራ ነው ብለዋል። እስካሁንም 3 ቢሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብ ከሕብረተሰቡ ማሰባሰብ መቻሉንም ነው የተናገሩት። ኅብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ያሳሰቡት።
ዶክተር ጌታቸው የመልካም አሥተዳደር ችግር በተለይም በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሕዝብን ያማረሩ ችግሮች እየታዩ ስለመኾንም አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት ከሥነ ምግባር እስከ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ክፍተቶች መኖራቸውን ከሚነሱ ቅሬታዎች ይረዳል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ፤ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሺን በጥናት ላይ ተመስርቶ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሥራ ላይ ነው ብለዋል።
ሙስና ላይ የተጀመረው ዘመቻ በሥራ ላይ እንደኾነም ነው የተናገሩት። ውጤቱን በጊዜው ማየት እንደሚቻልም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጣና ክፍለ ከተማ ለ258 አቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ፡፡
Next article“ቀንም አልነበረም፣ ሌሊትም አይደለም”