የጣና ክፍለ ከተማ ለ258 አቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ፡፡

54
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የጣና ክፍለ ከተማ 421 ሺህ ብር ግምት ያለው የበዓል መዋያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የትንሳኤ እና ኢድ-አልፈጥር በዓላትን ምክንያት በማድረግ የሚደረገው ድጋፍ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ይተገበራል ተብሏል፡፡
የ2015 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ እና የኢድ-አልፈጥር በዓላት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከሰሞኑ ይከበራሉ፡፡ በዓላቱን የየሃይማኖቶቹ አስተምህሮዎች በሚያዙት እና የኢትዮጵያዊ እሴት መገለጫ በኾነው አብሮነት በጋራ ማክበር ይገባል ያሉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶክተር) ናቸው፡፡
በከተማዋ የሚገኙ አቅመ ደካሞች በዓላቱን በተቻለ መጠን በደስታ እንዲያሳልፉ ሁሉም ክፍለ ከተሞች እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡
የድጋፉ ዓላማ ሁሉንም ድጋፍ የሚያሻቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች ማዳረስ ሳይኾን ሌሎች ከዚህ በጎ ተግባር ተምረው በመረዳዳት እንዲያሳልፉት ማድረግ ነው ያሉት ዶክተር ድረስ በጣና ክፍለ ከተማ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች የተሰበሰበው ድጋፍ ዛሬ ለወገኖቻችን ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ ቀናት በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ ስድስቱም ክፍለ ከተሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ ያደርጋሉ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፡፡
ጣና ክፍለ ከተማ በክፍለ ከተማው ለሚገኙ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 258 ወገኖች የትንሳኤ እና ኢድ-አልፈጥር በዓላት መዋያ ድጋፍ አድርጓል ያሉት የጣና ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዱኛ ተሾመ ናቸው፡፡
በክፍለ ከተማው ኮሚቴ ተቋቁሞ ድጋፍ ሲያሰባስብ ቆይቷል ያሉት አቶ አዱኛ 421 ሺህ ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ዶሮ፣ ዘይት እና ሽንኩርት ተገዝቶ የተሰጠ ሲኾን ለተወሰኑት የኀብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ የብር ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች ከድጋፉ በላይ ማሰቡ ብቻ የተለየ ትርጉም እንዳለው ገልጸው ድጋፍ ላደረጉላቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዋስ መከታ የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይቅርታ እንጠይቃለን”በሰሜን ወሎ የሚገኙ የፋኖ አባላት
Next articleክልሉ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለሱን የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር ገለጹ።