
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሀገር ጠንካራ የፀጥታ ተቋም ለመገንባት የሚሠራውን ሪፎርም በመቀበል ከምድብ ስፍራቸው ወደ ዞኑ የመጡ የቴዎድሮስ ክፍለጦር የልዩ ኀይል አባላትን የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ደማቅ አቀባበል አደርጎላቸዋል።
በአቀባበል መርሐ ግብሩ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጥላሁን ደጀኔ እንደተናገሩት አንድነትና ወንድማማችነት ለሀገር ህብረ ብሔራዊ አንድነት መውጫ በር ነው ብለዋል።
በሀገራችንና በክልላችን ዘላቂ በኾነ መንገድ የሕዝባችን አንድነት ለማስጠበቅ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሰሞኑን የልዩ ኀይል ሪፎርም ትግበራ አስመልክቶ በዞኑ አንዳንድ ከተሞችና አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ ተከስቶ እንደነበር ተናግረዋል። ችግሩን የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ልዩ ኀይሎች፣ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የጋራ ምክክር በማድረግ ወደነበረበት ሰላም እንዲመለስ ተደርጓል ነው ያሉት።
ሀገራችን ያለችበትበት ውስብስብ ችግር በተጣመረ ክንድና በአንድነት መንፈስ ችግሩን እንፈተዋለን ነው ያሉት። አቶ ጥላሁን ደጀኔ እንደ ሀገር ጠንካራ የፀጥታ ተቋም ለመገንባት መንግሥት ያቀረበውን የልዩ ኀይል ሪፎርም በመቀበል ሰላምን ለማስጠበቅ በሕጋዊ መንገድ ወደ ዞናችን የመጣችሁ የልዩ ኀይል አባላት በሙሉ እንኳን ደህና መጣችሁልን ብለዋል።
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ቤተሰቦቻቸውን ለተቀላቀሉ የልዩ ኀይል አባላቶችም በሚፈጠሩ ግልፀኝነትና መንግሥት ባወጣው የቅበላ አቅጣጫ መሠረት ለመቀበል በዞናችንና በክልላችን መንግሥት ስም ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።
የልዩ ኀይል አባላቶች እንደተናገሩት እስካሁን ለክልላችንና ለሀገራችን ሕዝብ እንዳገለገልነው ሁሉ በቀጣይም መንግሥት ባስቀመጠው የሪፎርም አቅጣጫ መሠረት በመቀላቀል ለሕዝባችን ሰላም ደምና አጥንታችን ሰጥተን እናገለግላለን ብለዋል።
በአቀባበል ፕሮግራሙም የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጥላሁን ደጀኔ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን የሕዝብ ሰላምና ደህንነት ኃላፊ አሸናፊ አግማስና ሌሎችም የፀጥታ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!