
ደሴ: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሚገኙ የልዩ ኀይል አባላት መካከል በደቡብ ወሎ ዞን የተመደቡ የልዩ ኀይል አባላት በ20 ወረዳዎችና በ9 ከተማ አሥተዳደሮች በፖሊስ፣ በማረሚያ ቤትና ሌሎችም ተቋማት ምደባ ተሠጥቷቸው ሽኝት ተደርጎላቸዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የልዩ ኀይል አባላትም መንግሥት ባስቀመጠው አዲስ አደረጃጀት መሰረት በተሰማሩበት አካባቢ ሕዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን ከማንኛውም ጥቃት ለመጠበቅ ዝግጁ መኾናቸውን የተናገሩት አባላቱ ልዩ ኀይል ተበተነ የሚለው መረጃ ከግንዛቤ እጥረት የተፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል ።
መንግሥት ለላቀ ተልዕኮ የክልል ልዩ ኀይሎችን መልሶ ማደራጀቱ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም በደስታ እንደተቀበሉና በሚሰጣቸው ሥምሪት ለመሥራት ፈቃደኛና ዝግጁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። አባላቱ እውነታው ተነግሯቸው በሚፈልጉበት ዘርፍ ከነትጥቃቸው ምደባ ተሰጥቷቸው መሠማራታቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት በሚያሠማራቸው ግዳጆች ሁሉ ለመሠማራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
የደቡብ ወሎ ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አህመድ መሐመድ ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ እንደ ሀገር አንድ ጠንካራ የሆነ የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት ያስችላል ነው ያሉት
ይህም በክልል ደረጃ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት ያደረጉበትና የጋራ መግባባት የተደረሰበት መሆኑንም ተናግረዋል። በቀጣይም በሐሰተኛ መረጃዎች ምክንያት ግጭት እንዳይከሰት ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንሠራለን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!