ʺየመጨረሻዋ ራት፤ ምስጢረ ቁርባን የተገለጠባት”

133
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የታደሉት ከጌታቸው ጋር ማዕድ ይቆርሳሉ፣ በጌታቸው እጅ የተባረከች ሕብስት ይታደላሉ፣ በጌታቸው እጅ የተባረከች ጽዋ ይቀበላሉ፣ ያቺም ሕብስት የዘላለም ሕይወት የምታሰጥ የጌታ ቅዱስ ስጋ ምሳሌ ናት፣ ያቺም ጽዋ የዘላለም ሕይወት የምታሰጥ የጌታ ክቡር ደም ምሳሌ ናት፡፡
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ገዳመ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር እና የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መምህር ዘላለም እንደነገሩን የታደሉት ከጌታቸው ጋር ቃል በቃል ይነጋገራሉ፣ የታደሉት ከጌታቸው ሥር ተቀምጠው ይማራሉ፣ የታደሉት ከጌታቸው ፊት ሥርዓትን ያውቃሉ፡፡ እርሱ በተመላለሰባቸው ጎዳናዎች ይመላለሳሉ፡፡
የታደሉ ደቀመዛሙርት ከጌታቸው ጋር ማዕድ ቆረሱ፣ የታደሉ ደቀማዛሙርት በጌታ የተባረከች ጽዋ አነሱ፡፡ በየጎዳናዎችና በአውራጃዎች ከእርሱ ጋር ተመላለሱ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የባረካት ራት ከራቶች ሁሉ ትበልጣለች፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የባረካት ጽዋ ከጽዋዎች ሁሉ ትበልጣለች፡፡ ያቺ ሕብስት ዝም ብላ ሕብስት አይደለችም፣ ነብስን ታለመልማለች፣ የዘላለምን ሕይወት ታሰጣለች፣ ያቺ ጽዋ ዝም ብላ ጽዋ አይደለችም፣ የዘላለምን ሕይወት ታስገኛለችና፡፡
ጸሎተ ሐሙስን ደቀመዛሙርቱ ከጌታቸው ጋር ማዕድ የተጋሩባት፣ ሕግና ሥርዓት ያዩባት፣ የብሉይ ዘመን ተፈጽሞ ሐዲስ ኪዳን የተጀመረባት፣ መስዋዕተ ኦሪት ተፈጽሞ፣ የሐዲስ ኪዳን መስዋዕት የተጀመረባት ዕለት ናት ይሏታል መምህር ዘላለም፡፡ ጸሎተ ሐሙስ የኢየሱስ ክርስቶስ የሕማማት ሳምንት ከሚታሰብባቸው ቀናት መካከል አንደኛዋ እንደኾነችም ያስረዳሉ፡፡
የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት ሰሞነ ሕማማት እየተባለች ትጠራለች፡፡ ሰሞነ ሕማማት የመከራ፣ የሕማም ሳምንት ማለት እንደሆነ የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ፡፡ በዐቢይ ፆም ሁሉም ሳምንታት የየራሳቸው ስያሜ አላቸው፡፡ ስያሜያቸውም ምስጢር የሚመሰጠርባቸው፣ ሃይማኖት የሚጸናባቸው ናቸው፡፡
የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር እና የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር ዘላለም በላይ በሰሞነ ሕማማት እያንዳንዱ ቀናት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰዓታት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚደረግባቸው፣ የጌታ ኢየሱስ ሕማማት የሚታሰብባቸው ናቸው ብለውናል፡፡ ይህችም ሳምንት በክርስቲያኖች ዘንድ በሀዘን፣ በበረታ ጸሎትና ስግደት ትታለፋለች፣ ብዙዎች በሰሞነ ሕማማት ጫማቸውን ከእግራቸው ላይ ያወጣሉ፣ እሾህና አሜካላ በበዛበት ምድር የጌታን ሕመም እያስታወሱ በባዶ እግራቸው ይመላለሳሉ፡፡ ስጋቸውን እያደከሙ ነብሳቸውን ያጠግባሉ፡፡ የጌታን ሕመም እያስታወሱ ይሰግዳሉ፣ ይጸልያሉ፡፡ እንባንም በጉንጮቻቸው ላይ ያፈስሳሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጌታ መከራ የተቀበለባቸው ናቸውና፡፡
በሰሞነ ሕማማት ክርስቲያኖች በዘመኑ እንደነበሩ ሆነው ያስቡታል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የመጨረሻው ራት እና የመጨረሻው ትምህርት የተደረገበት እንደሆነም መምህሩ ነግረውናል፡፡ በጸሎት ሐሙስ ቀን ጌታ ለደቀመዛሙርቱ ራት አበላቸው፣ ትምህርትም አስተማራቸው፡፡ ይህችም ራት የመጨረሻዋ ራት እየተባለች ትጠራለች፡፡
መምህሩ ቅዱስ መጽሐፍን ጠቅሰው እንዳስረዱት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት፡፡ እርሱም እነሆ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፡፡ ወደሚገባበት ቤት ተከተሉት፡፡ ለባለቤቱም መምህሩ ከደቀመዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፡፡ ያም በድርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፡፡ በዚያም አሰናዱልን አላቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፡፡ ፋሲካንም አሰናዱ፡፡ በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕዱ ተቀመጠ፡፡ ሲመገቡም እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ፡፡ እጅግም አዝነው ጌታ ሆይ እኔ እሆንን ይሉት ጀመር፡፡
እርሱም መልሶ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው፡፡ የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይኾናል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ፡፡ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ መምህር ሆይ እኔ እሆንን አለ፡፡ አንተ አልህ አለው፡፡ ሲመገቡም ኢየሱስ እንጀራን አንስቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሎ ይህ ስጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋንም አንስቶ አመሰግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፡፡ ስለብዙዎች ለኃጢያት ይቅርታ የሚፈስ የሀዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡
በዚህች ቀን ሥርዓተ ቁርባንን ሠራት፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረውን መስዋዕት ፈጽሞ በሐዲስ ኪዳን ራሱ መስዋዕት እንደሚሆን አስተማረ፡፡ ክቡር ደሙን የጠጣ፣ ቅዱስ ስጋውን የበላ የዘላለም ሕይወት እንዳለው አስተማራቸው፡፡ በዚያች ዕለት ሥርዓትን አስተማረ፣ ሕግንም አሰረ ብለዋል መምህሩ፡፡
ጸሎተ ሐሙስ ከብሉይ ኪዳን ሥርዓት ወደ ሐዲስ ኪዳን ሥርዓት የተሻገገረባት ስለሆነ የመሸጋገሪያ ቀን ትሰኛለች፡፡ ቅዱስ ቁርባንን የገለጠባት ቀንም ስለሆነች የምስጢር ቀን ትባላለች ብለውናል መምህር ዘላለም፡፡
ወደ ደብረ ዘይትም ወጡ፡፡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዚያች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፣ እረኛው ይመታል፣ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፏልና፡፡ ከተነሳሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው፡፡ ጴጥሮስም መልሶ ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው፡፡ ኢየሱስም እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው፡፡ ጴጥሮስም ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለው፡፡ ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ፡፡
ጌቴሰማኔ ወደ ምትባል ሥፍራም ሄዱ፡፡ ጌታም ጸለየ፡፡ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው፡፡ ጥቂትም ወደፊት አለፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ አባት ሆይ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ፡፡ ወደ ደቀመዛሙርቱም መጣ፡፡ ተኝተውም አገኛቸውና ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ አላቸው፡፡
ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና አባት ሆይ ይህችን ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደሆነ ፈቃድህ ትሁን አለ፡፡ ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፡፡ ደግሞም ትቷቸው ሄደ፡፡ ሦስተኛም ጸለየ፡፡ ከዚያም ወዲያ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጥቶ እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም እነሆ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢያተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል አላቸው፡፡ ቆየት ብሎም ተነሱ እንሂድ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል አላቸው፡፡
ይህንም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፡፡ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰይፍና ጎመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ጋር መጡ፡፡ አሳልፎ የሚሰጠውም የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና መምህር ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ሳመው፡፡ ኢየሱስም ወዳጄ ሆይ ለምን ነገር መጣህ፣ በመሳም አሳልፈህ የሰውን ልጅ ትሰጣለህን? አለው፡፡ በዚያን ጊዜ ቀረቡና ያዙት፡፡ ይህችም ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ የተሰጣባት ቀን ናት፡፡
በዚህች ቀን ክርስቲያኖች በጸሎተ ሐሙስ የሆነውን ሲያስቡና ሲጸልዩ ይውላሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቱ ተፈጽሞ ወደ ቤታቸው በተመለሱ ጊዜ ጉልባን ይመገባሉ፡፡ ጉልባን ከባቄላና ከሥንዴ ይዘጋጃል፣ ምዕመናንም ከቤተ ክርስቲያን እንደተመለሱ ሕማሙን፣ ስቃዩን መከራውን እያሰቡ ይመገቡታል ነው ያሉኝ መምህር ዘላለም፡፡ ይህም ጉልባንም ሊቃውንት ሲያመሰጥሩት ባቄላው ተከክቶ፣ ስንዴው ደግሞ ሳይከካ ይቀቀላል፡፡ በአንድ ላይም ይዋሃዳሉ፡፡ ይህም ባቄላው የኢሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ስጋው ተምሳሌት ሲደረግ፣ ስንዴው ደግሞ የመለኮቱ ተምሳሌት ይደረጋል ነው ያሉኝ፡፡
ባቄላው እንደሚከካ ሁሉ ክርስቶስም ቅዱስ ስጋው ተቆርሷልና፡፡ የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ላይ እንገኛለን፡፡ ክርስቲያኖችም የጌታቸውን ሕማም እያስታወሱ በጸሎት እየተጉ ነው።መልካም በዓል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ፎቶ፦ ከድረገጽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ማንኛውንም ጥያቄ በውይይት ብቻ መፍታት ተገቢ ነው” የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን
Next articleስፖርት ዜና: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ)