“ማንኛውንም ጥያቄ በውይይት ብቻ መፍታት ተገቢ ነው” የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን

155
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት በግላቸው ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በማወያየት ወደ መደበኛ የጸጥታ አደረጃጀት እንዲገቡ ወይም ደግሞ ወደ ቀደመ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም መሰረት በርካታ ግለሰቦች የክልሉን መንግሥት ጥሪ በመቀበል ሀሳቡን ተግባራዊ አድርገዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የታጠቁ የፋኖ አባላት ከሰሞኑ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የጸጥታ ችግር ተከስቶ ነበር። የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ጥረት የፋኖ አባላቱ ልባዊ ይቅርታ ጠይቀው ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የሰሜን ምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ብርሃኑ ጥላሁን የተከሰተውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሀገር ሽማግሌዎች የተጫወቱት ሚና ለሌሎች አካባቢዎችም ዓርአያ የሚኾን ነው ብለዋል። ግጭት ለማንም አይጠቅምም፣ ጥያቄዎችን በጠመንጃ ሳይኾን በውይይት ብቻ መፍታት ተገቢ ነው ብለዋል።
ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም መመሪያ እና ተግባር ሲወርድ በውይይት እና በመግባባት እንዲፈጸም እንጅ ወደ ሌላ መልክ በመቀየር አላስፈላጊ የጸጥታ ችግር ውስጥ መግባት አስፈላጊ አለመኾኑንም ገልጸዋል።
ፋኖ ምሬ ወዳጆ መከላከያ ሠራዊታችን እጅግ የምንወደው እና የምናከብረው የሀገር ተቋም ነው፤ ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ለተፈጠረው ግጭትም ይቅርታ ጠይቋል። በተፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ወገን ወንድሞቻችንን አጥተናል፤ ለዚህም ዋስ መከታ የኾነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይቅርታ እንጠይቃለን ብሏል። ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም፣ ለወደፊትም ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይት መፍታት ያስፈልጋል ሲልም ፋኖ ምሬ ገልጿል።
አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በፍጥነት ለማረም የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጾ ምስጋናም አቅርቧል። ፋኖ ምሬ በአባቶች ውይይት መሰረት የፋኖ አባላቱ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንደተመለሱ ጠቅሶ ለወደፊትም የሚነሱ ጥያቄዎች ካሉ በመነጋገር ብቻ መፈታት አለባቸው ብሏል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ቢሮ ኀላፊ ኮሎኔል ባምላኩ አባይ በሰሜን ወሎ ዞን የሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም መመለሳቸውን አድንቀዋል። በሌሎች አካባቢ ያሉ መሰል ግለሰቦችም ሰላማዊ ውይይት በማድረግ ወደመደበኛ ሕይወታቸው መመለስ አለባቸው ብለዋል።
በአሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ ሊቃነጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት የፀሎተ ሐሙስ በዓል እየተከበረ ነው፡፡
Next articleʺየመጨረሻዋ ራት፤ ምስጢረ ቁርባን የተገለጠባት”