“ሰሙነ ሕማማት” – የሕማማት ሳምንት

146
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት “ሰሙነ ሕማማት” በመባል ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የባሕርዳር ማዕከል ሰባኬ ወንጌል መምህር ለይኩን አዳሙ ከአሚኮ ኦንላይን ጋር ቆይታ አድርገው የሰሙነ ሕማማትን ምንነት እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎችን ነግረውናል። ሳምንቱ በዐቢይ ጾም መጨረሻ ከዕሑድ ጀምሮ እስከ ትንሣዔ ያሉ ቀናትን ያጠቃልላል።
እንደ መምህር ለይኩን ገለጻ ሰሙነ ሕማማት የሚለው ቃል “ሰሞን” እና “ሕማማት” ከሚሉ ሁለት ጥምር ቃላት የተመሠረተ ስም ሲሆን “ሰሙን” የሚለው ቃል ሰሞን ወይም አንድ ሳምንት ማለት ነው። ከዕሑድ እስከ ዕሑድ፣ ስምንት ቀን የሚል ትርጉም ያለው ሐሳብ ነው። “ሕማማት” የሚለው ደግሞ “ሐመ ታመመ” ከሚለው ከግዕዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲኾን ትርጉሙም ሕመሞች ፣ደዌዎች ፣መከራዎች ፣ስቃዮች ማለት ነው።
ስለዚህ ሰሙነ ሕማማት የሚለው ጥምር ቃል የሕማሞች ሳምንት የሚል ትርጓሜ ይኖረዋል። ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ ተይዞ ተገርፎ ፣ተሰቅሎ መሞቱን በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚታሰብበት ሳምንት ነው።
ከመጀመሪያው ዕሑድ እስከ ትንሳዔ ቀን ያሉ የሰሙነ ሕማማት ዕለታት የየራሳቸው ስያሜ አላቸው። መምህር ለይኩን በነገሩን መሰረት:-
👉 ዕሁድ – ይህች ቀን ሆሳዕና በዓርያም በመባል ትጠራለች። ሆሳዕና በዓርያም ማለት ከሰማይ የመጣ መድኃኒት ማለት ነው። በዚህ ዕለት ክርስቶስ የታሰረችን አህያ ከእስራቷ ፈትቶ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ሲኾን የኢየሩሳም ሰዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው የዘመሩበትና ያመሰገኑበት የምስጋና ቀን ነው። ዕለቱን እስከ አሁን ድረስም የእምነቱ ተከታዮች የዘንባባ ቅጠል በራስ ዙሪያ በማሰር ያከብሩታል።
👉 ሰኞ – እለቱ “መርገመ በለስ” በመባል ይጠራል።
በዚህ ዕለት አዳምና ሔዋን ከገነት እንደተባረሩ፣ የበለስ ቅጠል እንዳገለደሙ ይታሰባል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እንደጻፈው ኢየሱስ ክርስቶስ በበዓለ ሆሳዕና በመሸ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ኾነ ብሎ መጣ። የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። በዚያን ጊዜ “ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” ብሎ ረገማት። ስለዚህም በሰሙነ ሕማማት የሚገኘው ሰኞ “መርገመ በለስ” የተፈጸመበት ዕለት መታሰቢያ ነው። የዚህም ትርጉም ወይም ምሥጢሩ ከበለስ ፍሬ መሻቱ ከሰው ፍቅር ተርቦ ማጣቱን ለመግለጽ ነው፡፡ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ እንደሚቆረጥና ቅጠሎቹም እንዲቃጠሉ የተነገረውን በማስታወስ ሰው ሁሉ መልካም ፍሬን ሊያፈራ እንደሚገባ ለመግለጽም ታስቦ ነው።
👉 ማክሰኞ – “ዕለተ ጥያቄ” ወይም የጥያቄ ዕለት በመባል ይጠራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቅደስ ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሸማግሌዎች ወደ እርሱ ቀረቡና በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ይህንን ጥያቄያቸውን ኢየሱስም በጥያቄ ነበር የመለሰላቸው። በዚህ ዕለት የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ያቀረቡለትን ጥያቄ በጥያቄ የመለሰበት ቀን ስለኾነ የጥያቄ ዕለት ይባላል።
👉 ረቡዕ – ይህ ዕለት የምክረ አይሁድ ዕለት ነው።
የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እንዲሁም ጸሐፍት ፈሪሳውያን ክርስቶስን ለመግደል የመጨረሻውን ምክክር ያደረጉት ከዕለተ ሆሳዕና ማግስት በሚውለው ሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ ነበር። ሰኞና ማክሰኞ ይሰቀል፣ አይሰቀል በሚለው ክርክር ከውሳኔ ሳይደርሱ ተበትነዋል ። በመጨረሻም በዕለተ ረቡዕ ይሰቀል፤ ይገደል በሚለው ተሰማምተውበታል ። በዚህም የተነሳ ዕለተ ረቡዕ “ምክረ አይሁድ” ይባላል።
ሌላው በዕለተ ረቡዕ የተፈጸመው ተግባር መላ ዘመኗን በዝሙት ኃጢአት ያሳለፈች ሴት ወደ ክርስቶስ መጥታ ስለኃጢአቷ ይቅርታ በኢየሱስ እግር ሥር ተደፍታ ማልቀሷ የሚታሰብበት ዕለት ነው። በዚህ እለት ይሁዳ ክርቶስን አሳልፎ ሊሰጥ በ30 ብር ተደራድሮ የተስማማበትና የተዋዋለበት ዕለትም ነው።
👉 ሐሙስ- ይህ እለት “ጸሎተ ሐሙስ” ይባላል። በሰሙነ ሕማማት የምትውለው ዕለተ ሐሙስ በተለያዬ መጠሪያዎች ትጠራለች። ጸሎተ ሐሙስ፣የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፣የነጻነት ሐሙስ፣ ሕጽበተ ሐሙስ፣ የምሥጢር ቀን ፣አረንጓዴ ሐሙስ በመባል ትጠራል።በአጠቃላይ ይህ ቀን ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትህትናን ያስተማረበት ዕለት ነው።
👉 ዓርብ – ዓርብ የስቅለት እለት ትባላለች።አዳም ክፉ ምክር ሰምቶ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን ቀጥፎ በልቶ ከክብሩ የተዋረደውና ሞት ተፈርዶበት ከገነት የተሰደደው በዚሁ በዕለተ ዐርብ ነበር። ይህ ዕለት አዳምና ልጆቹን ነጻ ለማውጣት ዳግማይ አዳም ክርስቶስ የበረከት እጆቹ እና የሰላም እግሮቹ የተቸነከሩበት፤ ለሰው ልጆች ሲል ነፍሱንም በፈቃዱ አሳልፎ የሰጠበት ነው። በመኾኑም “የድኅነት ቀን” እና “መልካሙ ዓርብ” በመባልም ይጠራል።
👉 ቅዳሜ – ዕለቱ “ቅዳም ሥዑር” ይባላል። ቅዳም ሥዑር ማለት “የተሻረ ቅዳሜ” ማለት ነው።ይህ ዕለት የተሻረው በጾም ነው። ከዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በሰሙነ ሕማማት ውስጥ በምትገኘዋ ቅዳሜ የእምነቱ ተከታዮች በጾም እንዲያሳልፉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርታለች። ሥዑር መባሏም ለዚህ ነው። በዚህ ዕለት ካህናት ለምለም ቀጤማ ለምዕመናን ያድላሉ። ለምለም ቀጤማ ማደላቸው ክርስቶስ ስለሰዎች በመስቀል ተሰቅሎ በመሞቱ ለዘመናት በሙሉ በሰው ልጆች ላይ የተፈረደው ሞት መወገዱን ለማብሰር ነው።
👉 ዕሁድ – ፋሲካ ወይም ትንሣዔ በመባል ትጠራለች
ፋሲካ ማለት “አለፈ” ማለት ነው። መርገም፣ ሞት፣ ባርነት፣ ጨለማ ፣ድንቁርና በአጠቃላይ ክፉ አገዛዝ የተሻረበት እና የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤው የተረጋገጠበት ልዩ የደስታ ዕለት ማለት ነው።
ለእምነቱ ተከታዮች በሙሉ መልካም የትንሳዔ በዓል ይሁንላችሁ! ለኢትዮጵያዊያን መጭው ዘመን ሁሉ የደስታ ይሁን!
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበልና ይፋዊ ይቅርታ በማቅረብ ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ ተስማሙ።
Next articleየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ ሊቃነጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት የፀሎተ ሐሙስ በዓል እየተከበረ ነው፡፡