በተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ እና በድርቅ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመቅረፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

341

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የአንበጣ መንጋ ተከስቷል፤ በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በማዕከላዊና በሰሜን ጎንደር ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ደግሞ ድርቅ ተከስቷል፡፡ የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች አንበጣው ሁሉን አውዳሚ ስለሆነ የእንስሳት መኖ ላይም ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡

ስለጉዳዩ ምን ያክል ትኩረት ተሰጥቶታል ስንል የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጄንሲን ጠይቀናል፡፡ በኤጄንሲው የመኖ ልማትና አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አበበ ምትኬ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት የአንበጣ መንጋ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የመኖ እጥረት ሊፈጠር ስለሚችል ከግብርና ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በደረሰባቸውና ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሊፈጠር የሚችለውን የመኖ እጥረት ታሳቢ በማድረግ ምን ያክል ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተጎዱ? የትኞቹ የእንስሳት ዓይነቶችስ የበለጠ ተጎጂ ይሆናሉ? የሚለውን የመለየት ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተለይም የአንበጣ መንጋው የተከሰተው መኖ ከመሰብሰቡ በፊት መሆኑ ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል›› ተብሏል፡፡

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የመኖ ችግር ለመፍታት ጉዳቱ ከሌሎች አካባቢዎች የተሰበሰቡ መኖዎችን በመግዛት ለማቅረብ እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የትራንስፖርትና የግዥ አቅርቦቱን የሚያግዙ ድርጅቶች ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአንበጣ መንጋውን በመቆጣጠር ሂደትም እስከ ቀበሌ ድረስ በሚገኙ የእንስሳት ሀብት ጽሕፈት ቤቶች አማካኝነት ማኅበረሰቡን በማስተባበር እየተሠራ ነው›› ብለዋል፡፡ ኤጀንሲው ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ ከአደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን እና ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ጭምር ግብረ ኃይል በማቋቋም እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ከመኖ አቅርቦት ባለፈ እንስሳትን በሽያጭ የመቀነስ ሂደት እንዲኖር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አቶ አበበ አስታውቀዋል፡፡ በመኖ እጥረት ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን የእንስሳት በሽታ ለመከላከል የሚያስችል መድኃኒት ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እተደረገም እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ችግሩ በተከሰተባቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም መኖን በመስኖ የማልማት ሥራዎች እንደሚሠሩ አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ በችግሩ ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸውን እንስሳት ሙሉ ለሙሉ ማጥገብ ባይቻል እንኳን ከአደጋው እንዲተርፉ የማድረግ ሥራው በትኩረት እንደሚሠራበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም ሥርዓት በሀገሪቱ ለሚታየው አለመረጋጋት ዋነኛ መንስኤ መሆኑ ተገለጸ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት ከሕግ አስፈጻሚ፣ ሕግ ተርጓሚ አካላትና ከሕዝብ ክንፍ መሪዎች ጋር እየተወያዬ ነው፡፡