
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ትሁቶች ትሕትናን ያስተምራሉ፣ ደጎች ደግነትን ያሳያሉ፣ ልበ ቀናዎች የተወደደውን ያደርጋሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥት ኾኖ ሳለ እንደ አሽከር አገለገላቸው፣ አምላክ ሆኖ ሳለ እንደ አሽከር ዝቅ ብሎ እግራቸውን አጠባቸው፡፡ ደግ ነውና እግሩን ሊያጥቡት፣ እነርሱ ዝቅ ብለው እርሱን ከፍ ከፍ ሊያደርጉት ሲገባ እርሱ ግን ዝቅ ብሎ እግራቸውን አጠባቸው፣ ትህትናን አስተማራቸው፡፡ መልካምነትን አሳያቸው፡፡
ብዙዎች የእርሱን የክብር ልብስ ለመንካት ተጣድፈዋል፣ ከእርሱ ጋር በአውራጃዎች ተመላልሰዋል፤ የሚጣፍጥ አንደበቱን ለመስማት ተቻኩለዋል፣ በሰሙትም ጊዜ ደስ ተሰኝተዋል፣ ብዙዎች ድውያነ ስጋን በታዓምራት፣ ድውያነ ነብስን በትምህርት ሲያድናቸው ተገርመዋል፣ ተደንቀዋል፡፡ የተከተሉትና አብዝተው ያመኑትም ድነዋል፡፡ የእርሱን ልብስ የነኩም የተመረጡ ናቸው፡፡
እርሱ እግራቸውን ያጠበላቸው፣ ዝቅ ብሎ ትህትናን ያስተማራቸው ግን እንደምን የታደሉ ናቸው? እንደምንስ የተመረጡና የተወደዱ ናቸው? የተቀደሱ እጆቹ ዳብሰዋቸዋል፣ የተቀደሱ እጆቹ አጥበዋቸዋልና፡፡
የክርስትና እምነት ቅዱሳት መጽሐፍት እንደሚያትቱት እርሱ ዓለምን ይወስናታል እንጂ አትወስነውም፣ ዘመንን ይገዛል እንጂ በዘመን አይገዛም፣ ዘመነኞች በዘመን ተወስነው ይነግሳሉ፣ በዓለም ተወስነው ይገዛሉ፣ እርሱ ግን ገዢዎችን ይገዛል፣ ዘመንንም ይለካል፣ ይገዛል፣ ዘመን በማይቆጠርለት ንግሥና ለዘለዓለም ይነግሳል፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ፣ ዘመን ከመቆጠሩ አስቀድሞ ነበረ፡፡ ዓለምንም ፈጠረ፣ ዓለምንም አሳልፎ ይኖራል፡፡ ዓለምን ያሳልፋታል እንጂ አታሳልፈውም፣ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም እንዳለ፤ እርሱ አያልፍም፣ እንደነበረ፣ እንደአለ ይኖራል እንጂ፡፡
በብሉያትና በሐዲሳት እንደተጻፈው መላዕክት ክንፋቸውን እያማቱ የሚያመሰግኑት፣ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሚሰግዱለት፣ እየተፋጠኑ የሚታዘዙለት፣ ቅዱሳን ስለ ስሙ ዓለምን የሚንቁት፣ ስለ ፍቅሩ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊትን ታግሰው የሚኖሩለት፣ ሰማዕታት ስለ ፍቅሩ ሞትን የሚንቁለት፣ በሞት መካከል እየተመላለሱ ስሙን የሚጠሩለት፣ ክብሩን የሚገልጡለት፣ ነቢያት አስቀድመው የተነበዩለት፣ ስለ ኃያልነቱ፣ ስለ ቅድስናው የተናገሩለት፣ ሐዋርያት በዓለም ዙሪያ የሰበኩለት፦ አምላክ ዝቅ ብሎ የሰውን እግር አጠበ፡፡ አምላክ ሆኖ ሳለ ዝቅ ብሎ የሰውን እግር ማጠብ እንደምን ያለ ትህትና ነው? እንደምን ያለስ መልካምነት ነው? የእርሱን መልካምነት አንደበቶች አይገልጹትም፣ ልቡናዎች አይመረምሩትም፡፡ እጹብ ድንቅ እያሉ ያመሰግኑታል እንጂ ይላሉ የእምነቱ አባቶች፡፡
ይህስ ድንቅ ነው፣ ይህስ ግሩም ነው፣ እርሱን ማጠብ መታደል ሳለ እርሱ ግን አጥቧቸው ሕግና ሥርዓትን፣ ትህትና እና ፍቅርን አስተማራቸው፡፡
ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።የወደዳቸውንና የመረጣቸውንም አከበራቸው።
እራትም ሲበሉ ልብሱንም አኖረ፡፡ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፡፡ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፡፡ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ።
ወደ ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም ጌታ ሆይ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፡፡ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው። ጴጥሮስም የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም አለው። ኢየሱስም ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት። ጴጥሮስም ጌታ ሆይ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው። ኢየሱስም የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፡፡ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፡፡ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፡፡ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፡፡ እንዲህም አላቸው። ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረኩ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።
እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ላይ በስፋት ይገልጻል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ፣ ዝቅ ብሎም ትህትናን አስተማራቸው፡፡ እርሱ ደቀመዛሙርቱን እግራቸውን እንዳጠባቸው ሁሉ አበው ዛሬም ድረስ በጸሎተ ሐሙስ ዝቅ ብለው እግር ያጥባሉ፡፡ ከጌታቸው የተማሩትን ትህትና በቀና ልብ ይፈጽማሉ፡፡
በውቅያኖስ ላይ የሚረማመደው አምላክ ዝቅ ብሎ እግር አጠበ፡፡ በባሕር ዳር ሀገረ ስብክት ገዳመ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር እና የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መምህር ዘላለም በላይ በጸሎተ ሐሙስ እኔ እንዳደረኩ እናንተም አድርጉ ብሎ ታላቅ ትህትና ያስተማረባት የትህትና ቀን እየተባለች የምትጠራ ቀን ናት ብለውኛል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረውና ሕግና ሥርዓት እንዳስቀመጠው ሥርዓቱን ትተገብረዋለች ነው ያሉኝ፡፡ በጸሎተ ሐሙስ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ጳጳሳትን፣ ጳጳሳት ካህናትን፣ ካህናት ዲያቆናትን፣ ምዕመናንን ዝቅ እያሉ ያጥባሉ፡፡ ጌታ እንዳደረገው እነርሱም ትህትናውን በተግባር ይገልጻሉ፡፡
በጸሎተ ሐሙስ መታዘዝ የሚገለጥበት፣ ትህትና ያለበት፣ አክብሮት የሚታይበት በዝቅታ ውስጥ ከፍታ ያለበት ቀን ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የጌታ ትህትና የሚታሰብበት፣ ክርስቲያኖች ትህትናን የሚማሩበትና የሚያስቡበት ነው፡፡ እግር ማጠብ ዝቅ ማለትና መገልገል ነው፡፡ ክርስቲያኖች የፈጣሪያቸውን እና የአምላካቸውን አርዓያነት ይከተሉ ዘንድ ግድ ይላል ነው ያሉት፡፡
እኔ ልብለጥ እኔ ልብለጥ ከማለት እርሱ ይብለጥ፣ እኔ አውቃለሁ ከማለት እርሱ ያውቃል ማለትን መማር፣ ከእኛ ሌሎች እንደሚሻሉ ማመን አለብንም ነው ያሉኝ፡፡ በጸሎተ ሐሙስ ፍጹም ትህትና የታየበት ነውና የጌታን ትህትና ተማሩ ነው ያሉት፡፡
ጌታ ኢየሱስ በጸሎተ ሐሙስ አሳልፎ የሚሰጠውን የአስቆሮቱ ይሁዳን እግርም አጥቧል፡፡ የእርሱ ትህትና ወሰን የለውምና የከዳውን፣ አሳልፎ የሚሰጠውን አስቀድሞ አውቆት እያለ እርሱ ግን ተንበርክኮ እግሩን አጠበው፡፡ የእርሱ ትህትናም እጹብ ድንቅ ነውና የሚወዱትን ብቻ ሳይሆን የሚክደውንም አጥቧል፡፡
ክርስቲያኖችም ትህትናን ለሁሉም ያደርጉ ዘንድ ከኢየሱስ ይማሩ ዘንድ ግድ ይላቸዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ጌትነት፣ መምህርነት፣ ንጉሥነት ማገልገል እና ትህትናን ያስተማረባት ምስጢራዊት ቀን ጸሎተ ሐሙስ፤መልካም በዓል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ፎቶ፦ ከድረ ገጽ