
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ይጫወታሉ።
በደረጃ ሰንጠረዡ ሃዋሳ ከተማ በ28 ነጥብ አራተኛ ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ በ21 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሃዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ወልቂጤ ከተማ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሶስት ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ 4 ለ 3 ማሸነፉ ይታወቃል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ከምሽቱ 12 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሲዳማ ቡና በ20 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ሲገኝ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በ25 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ አሸንፎ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ አጋርቷል።
ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሐ-ግብር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐግብር እስከ ሚያዚያ 8 2015 ይቆያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!