“ሰሙነ ሕማማት ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም የሚጸለይበት፣ ስለ ፍቅርና አንድነት የሚሰበክበት፣ ሁሉም ወደ ፈጣሪ ድምጹን የሚያሰማበት ነው” መልዓከ ምሕረት ግሩም አለነ

53
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሃይማኖታዊ አስተምሕሮው የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀልና መከራን መቀበል ዋጋው ለሰው ልጆች ድኅነት ነው። እናም በሰሙነ ሕማማት ሰዎች ለተደረገላቸው ነገር ሁሉ በፆም፣በፆሎት እና በስግደት ምስጋናቸውን፣ፍቅራቸውን ለአምላካቸው በተግባር ለመግለጽ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚፈቅደውን ሁሉ ይከውናሉ።
መልዓከ ምሕረት ግሩም አለነ በባሕር ዳር ሀገረስብከት የደብረቅዱሳን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን አሥተዳዳሪ ናቸው። ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰሙነ ሕማማት ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ የከፈለው ዋጋ የሚታሰብበት ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
ታዲያ የሚደረገው ፆም፣ፆሎትና ስግደት ለክርስቶስ ክብርና ግብር በሚመጥን መልኩ ፣የእኛን አማኞችንም በሚጠበቅብን ምግባርና ክብር ልክ መገኘትን በሚያሳይ መልኩ መኾን እንዳለበት ይመክራሉ።
ሰሙነ ሕማማት ሳምንቱ በሦስት መሪ ጉዳዮች ማለትም በፆም፣በፆሎትና በስግደት ይከወናል የሚሉት መልዓከ ምህረት ግሩም አለነ፤ የትንሳዔ በዓል ማዕከል የኾነው ሰሙነ ሕማማት ከሃይማኖታዊ ክዋኔውም ባሻገር ማኅበረሰባዊ፣ሀገራዊ እና ገብረገባዊነትን የተላበሱ ትርጉም ያላቸው መልካም ነገሮች ሁሉ የሚከወኑበት እንደኾነ ያስረዳሉ።
ሰሙነ ሕማማት ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም የሚጸለይበት፣ ስለ ፍቅርና አንድነት የሚሰበክበት፣ ሁሉም ወደ ፈጣሪ የሚጮህበት እንደኾነም ነው የሚያስገነዝቡት።
እርስ በርስም በመተሳሰብና በመረዳዳት ፣ ፈጣሪ የሚወደው መልካም ሥራ በመስራት ፣ የሕዝብንና የሀገርን ሰላም በመጠበቅ ስሙነ ህማማትን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። አማኞች በዘወትር መስተጋብራቸው መልካም እና ከአምላካቸው የማያርቃቸውን ግብር ማሳየት አለባቸው ብለዋል።
መልዓከ ምሕረት ግሩም እንደሚያስረዱት ፆማችን ፣ ፆሎታችን እና ስግደታችን እንዲሰምር፣ልመናችንም እንዲሰማ የምግባር እና የተግባር ሰዎች መኾን ይገባናል።
ሲፆም፣ሲጸልይና ሲሰግድ ውሎ ከቤተክርስቲያን መልስ ከልኩ በወጣ ምግባር መገኘት አይገባም ሲሉም ያሳስባሉ። “አምላካችን ክርስቶስ ስለሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ ስናስብ በሚገባን ምግባርና ክብር ልክ ኾነን መገኘት አለብን” ሲሉም መልዓከ ምሕረት ግሩም አለነ በአጽንኦት ይመክራሉ።
በተለይም እንደ ሀገር ፈተና ውስጥ ባለንበት ወቅት ሰው ሁሉ እንደየ ሃይማኖቱ ለአምላኩ የሚታመንበት፣ለሕሊናውም የሚገዛበት የተግባር ሰው፣ ትህትናን የተላበሰ እንቅስቃሴ የሚያሳይበት መኾን ይገባዋል ብለዋል።
በቤተክርስቲያን ሰሙነ ሕማማትን በፆም፣ በፆሎትና በስግደት ላይ ያገኘናቸው አማኞች በሰጡት አስተያየትም ክርስቶስ ለሰው ልጆች መከራን ተቀብሏል ፤ ትህትናን፣ ፍቅርን አስተምሮናልና አርአያነቱን መውሰድም የሰው ልጆች ሁሉ ኀላፊነት ነው ብለውናል ። እኛም የተደረገልንን አስበን ለሰው ልጆች ፍቅርና መደጋገፍን በመተግበር ማሳየት አለብን ነው ያሉት።
ፈጣሪ እንዲሰማን የሚሰማ ጥሪ፣የሚደመጥ ልመና ማቅረብ ይገባል የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ እንደሀገር ለገጠሙ ችግሮች እና ሀገራዊ ፈተናዎች ሁሉ ለመፍትሔ መጾም እና መጸለይን እንደመረጡ ነው የነገሩን።
ፈጣሪ ከክፉ ድርጊቶች ሁሉ እንዲጠብቀን፣ሀገርና ሕዝቡን ሁሉ ከጥፋት እንዲታደግ፣ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን የምሕረት እጁን እንዲዘረጋ በቅን ልቦና፣በስክነት መጸለይ ይገባል መልዕክታቸው ነው።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ማኀበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም የመረዳዳት ባሕላችንን ልናጎለብት ይገባል” መላከ ገነት ደጀን ተስፋዬ
Next articleየ19ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።