“ማኀበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም የመረዳዳት ባሕላችንን ልናጎለብት ይገባል” መላከ ገነት ደጀን ተስፋዬ

138
ከሚሴ:ሚያዝያ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በከሚሴ ከተማ ተስፋ ነዳያን የተሰኘ ማኀበረሰብ አቀፍ የልማትና በጎ አድራጎት ማኀበር ለትንሳዔ በዓል ለአቅመ ደካሞች መዋያ በማኀበራዊ ሚዲያ 350 ሺህ የሚጠጋ ብር ከማኀበሩ አባላትና ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች መሰብሰብ ችሏል::
የማኀበሩ የበላይ ጠባቂና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የከሚሴ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከ ገነት ደጀን ተስፋዬ በአሁኑ ሰዓት ባለው የኑሮ ውድነትና የሰላም እጦት ምክንያት በየአከባቢያችን በርካታ አቅመ ደካሞች እና በከፋ ችግር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን መርዳት ሃይማኖታዊ ግዴታችን ነው ብለዋል::
ይህንን መሻገር የሚቻለው ደግሞ የመረዳዳት ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ከመቸውም ጊዜ በላይ በማጠናከር ነውም ሲሉ ተናግረዋል:: ማኀበራዊ ሚዲያ ደግሞ በቀላሉ የመረዳዳት ባሕላችንን ያለ ገደብ ለማስፋትና ለማጎልበት ምቹ መደላድል በመኾኑ ለመልካም ዓላማ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል መላከ ገነት ደጀን።
የማኀበሩ የበላይ ጠባቂ መላከ ገነት ደጀን ተስፋዬ በማኀበራዊ ሚዲያ በተሰባሰበው ሀብት አካል ጉዳተኞችን፣ ህሙማንን፣ ደጋፊ የሌላቸውና በችግር ውስጥ የሚገኙ 160 አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ ለበዓል መዋያ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ብለዋል::
የበጎ አድራጎት ሥራ ዘርና ሃይማኖት የማይገድበው በምድር ተወዳጅ ፤ በፈጣሪም የታዘዘ ቅዱስ ተግባር ነው ያሉት መላከ ገነት ደጀን በድጋፉ ከክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ባሻገር ወቅቱ የረመዳን ወቅት በመኾኑ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ አቅመ ደካሞችንም ማካተት ስለመቻሉ ነግረውናል::
የማኀበሩ የበላይ ጠባቂ መላከ ገነት ተስፋዬ ማኀበሩ አሁን ካደረገው ድጋፍ ባሻገር በበዓሉ እለት የማኀበሩ አባላትና አባቶች በአቅመ ደካሞች እና ለሀገር ውለታ በዋሉ አረጋውያን ቤት በመሄድ በዓሉን ከእነዚህ ወገኖቻችን ጋር እንደሚያከብር ተናግረዋል፡፡
ሕዝበ ክርስትያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ፣ የታመሙ፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመጠየቅና በመርዳት እንዲኾን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል::
ማኀበሩ በድጋፉ ከከሚሴ በተጨማሪ የወለዲና ጨፋ ሮቢት ከተሞች አቅመ ደካሞችንም ለመድረስ የቻለ ሲኾን የድጋፉ ተጠቃሚዎች በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጎ ፈቃደኞችንም አመስግነዋል::
ዘጋቢ:- ስነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየቅጥር ፈተና ዉጤት ስለማሳወቅ
Next article“ሰሙነ ሕማማት ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም የሚጸለይበት፣ ስለ ፍቅርና አንድነት የሚሰበክበት፣ ሁሉም ወደ ፈጣሪ ድምጹን የሚያሰማበት ነው” መልዓከ ምሕረት ግሩም አለነ