
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል። የክልል ልዩ ኀይሎችን መልሶ ለማደራጀት ሲታሰብ የአማራ ክልል መሪዎች ብቻቸውን የወሰኑት አይደለም ብለዋል። ውሳኔው የሀገር አርማ የተላበሰ ጠንካራ የመከላከያ ኀይል ለመገንባት ያለመ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
በዚህ የጋራ ውሳኔ መሰረት የአማራ ልዩ ኀይልም ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ በመቀላቀል የተለመደ የሀገር ዘብነት ተግባሩን እንዲያስቀጥል ነው የተፈለገው ነው ያሉት።
“አንድነቷ የጸና እና የታፈረች ኢትዮጵያን ለመገንባት አንድ ዓይነት የሀገር ዓርማ የተላበሰ ኃይል ያስፈልገናል” ሲሉም ገልጸዋል።
የክልል ልዩ ኀይሎችን መልሶ በማደራጀት ጠንካራ የሀገር የጸጥታ ኀይል ለመፍጠር የታመነበትን ውሳኔ ለመቀልበስ ውዥንብር የሚፈጥሩ አካላት ስለመኖራቸውም ዶክተር ሰማ ገልጸዋል።
ውሳኔውን በውል ባለመገንዘብ ከካምፕ የወጡ የልዩ ኀይል አባላትን እውነቱን አሳውቆ የሚያሰባስብ ግብረ ኀይል በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ላይ ተቋቁሞ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የአማራ ልዩ ኀይል ክልሉ ብሎም ሀገር ችግር ላይ በወደቀበት ወቅት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን መስእዋትነት ከፍሎ ሀገር ያቆመ የታሪክ ባለቤት ስለመኾኑም ገልጸዋል። ልዩ ኃይሉ ውዥንብር የሚፈጥሩ አካላትን አሉባልታ ወደ ጎን በመተው መልሶ ወደ ማደራጀት የላቀ የሀገርንና ሕዝብን ሰላም የማስጠበቅ ተልዕኮ መቀላቀል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ዶክተር ሰማ “የልዩ ኀይል አባላት ትጥቃቸውን አስረክበው እንዲበተኑ ሳይኾን የያዙትን ትጥቅ አስመዝግበው ወደላቀ ተልዕኮ እንዲሸጋገሩ ነው የተፈለገው” ብለዋል። ይህም ሲኾን የአማራ ልዩ ኀይል ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመኾን የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የሚችል ጀግና ኀይል ስለመኾኑ ታምኖበት ነው ብለዋል።
የአማራ ክልልን ሕዝብ ብሎም የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ከክልል ልዩ ኀይልነት ከፍ በማለት ሀገራዊ የጸጥታ መዋቅሮችን መቀላቀል እንደሚያስፈልግ ለልዩ ኀይል አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተወሰነውን ውሳኔ በውል ባለመረዳት ከሰሞኑ የተፈጠረውን የሕዝብ ስሜት ለማረጋጋት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደነበር ዶክተር ሰማ ጠቅሰዋል። ወጣቶች ላሳዩት ስክነት እና ስልጡንነትም ምስጋና አቅርበዋል።
ዶክተር ሰማ ወደ አላስፈላጊ የሰላም መደፍረስ ከመግባት በፊት ውይይቶችን ማድረግ እና መግባባት መቻል መልካም መኾኑን ተናግረዋል።
አሁን ያለውን ድባብ ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም በመቀየር በቀጣይ የሚከበሩ የክርስትና እና የእስልምና በዓላትን በሰላምና በፍቅር ማሳለፍ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!