“በደሴ ከተማ በከፍተኛ ወጭ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በሰላም እጦት ምክንያት እንዳይስተጓጎሉ ሕብረተሰቡ ኀላፊነቱን መወጣት አለበት” ከተማ አስተዳደሩ

144
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ ሰላም እና ልማት ቀጣይነት እንዲኖረው ማኅበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ጥሪ አቅርበዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ አሁን ላይ
በከተማዋ ሰላማዊ የነዋሪዎች እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል።
በከተማዋ ሚያዝያ 02/2015 ዓ.ም የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ሳሙኤል ሕዝቡ በሰላም ድምጹን አሰምቷል ነው ያሉት። በዛሬ ውሎም በከተማዋ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
የትንሣዔ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት የተቃረቡበት በመሆኑ ኅብረተሰቡ በዓላቱን በሰላማዊ መንገድ ለማክበር መዘጋጀት ነው ያለበት ብለዋል።
ወቅቱ ክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች የፆምና የፀሎት ወቅት በመሆኑ ሁሉም በየእምነቱ ለሀገር ሰላም እንዲፀልይም ጥሪ አቅርበዋል።
በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ማሽነሪዎችን በከፍተኛ ወጪ ተከራይቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀው በሰላም እጦት ምክንያት የልማት ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ ሕብረተሰቡ የድርሻውን ኀላፊነት እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የደሴ ከተማ የንግዱ ማኅበረሰብ ለፋሲካ እና ለኢድ አልፈጥር በዓላት የፍጆታ ምርቶች የአቅርቦት ችግር እንዳይኖር ከወዲሁ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:–ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የልዩ ኀይል ሪፎርም የሚካሄደው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ የሀገርን አንድነት የሚያጸና ጠንካራ የጸጥታ ኀይል ለመገንባት ነው” አቶ ግርማ የሺጥላ
Next articleንግድና ምጣኔ ሃብት ዜና: ሚያዝያ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ)