“የአማራ ልዩ ኃይልን በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን የተወሰነ ውሳኔ የለም” ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

454

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል።

መግለጫቸውም በሀገር ደረጃ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ለማደራጀት መወሰኑን ተናግረዋል። ወደ ትግበራም መገባቱን ገልፀዋል።

ውሳኔው በፌዴራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት ስምምነት የተወሰነ መሆኑንም ተናግረዋል።በአማራ ክልልም ውሳኔውን ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን ያነሱት።በአፈጻጸም ላይ በታየ ክፍተት እና በተነዛው ፕሮፖጋንዳ ችግሮች መከሰታቸውንም ተናግረዋል፡፡ችግሮችንም ተወያይቶ መፍታት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

ጀግና ልዩ ኃይል ነው፣ መስዋእትነት የከፈለ ልዩ ኃይል ነው፣ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ሆኖ የሀገርን ሕልውና እና ሉዓላዊነት የጠበቀና ያስከበረ ነው፣ ይህ ልዩ ኃይል ትጥቅ የሚፈታና የሚበተን አይደለም፣ በላቀ አደረጃጃት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡

ልዩ ኃይሉ ዓላማውን ተገንዝቦ ለበለጠ ተልእኮ እንዲዘጋጅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዓላማው የሀገር አንድነትን የሚያጸና፣ አብሮነትን የሚያስቀጥል እና የጸጥታመዋቅሩ በክልልም ሆነ በፌዴራል የተናበበና ሕግን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ማድረግ ነውም ብለዋል፡፡

አደረጃጀቱ የአማራን ክልል በተለየ መንገድ የሚጎዳ አይደለም ብለዋል፡፡በተፈጠረው የመረጃ ክፍተት በአንዳንድ ከተሞች የሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴ፣ የአድማ ጥሪ እና የሰዎች እና የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴን የመገደብ አዝማሚያዎች እያታዩ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡አላስፈላጊ አካሄዶች አውዳሚ እና አክሳሪ እንጂ አትራፊ አለመሆናቸውንም አንስተዋል፡፡በመወያየት አላስፈላጊ ጉዳዮችን ማስቆም እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

ሁሉም አውዳሚ የሆነውን ጉዳይ መከላከል እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡በረጅም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪኩ እና በስርዓት አክባሪነቱ የሚታወቀው የአማራ ሕዝብ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማየት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ችግሩ ዳር ወጥቶ ግጭት እንዳይከሰት እያደረጉ ላሉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡በመደማመጥ ችግሮቻችን እንፈታለን፣ የአማራን ጥያቄዎች እናስመልሳለንም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከጊዜያዊ መፍትሄ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next article“ኢትዮጵያ መሠረታዊ ውጪዋን ለመሸፈን ግብርን በአግባቡ መሠብሰብ እና ከአጋር አካላት ጋር በጥምረት መሥራት ይገባል” የገቢዎች ሚኒስቴር