
ባሕርዳር: መጋቢት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ወጥ የኾነ ሀገራዊ የጸጥታና ደህንነት ኃይል እንዲኖር የሚያደርገውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ መጀመራቸውን የክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊዎች ተናገሩ።
የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅ እንጂ ትጥቅ የማስፈታትና የመበተን ዓላማ እንደሌለውም ገልጸዋል።
የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እየተከናወነ የሚገኘውን ሥራ አስመልክቶ የፌደራልና የክልል የጸጥታ ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት አካሄደዋል።
በውይይቱም የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የክልል ሰላም፣ ደህንነትና የሚሊሻ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የሚሊሻና የልዩ ኃይል አዛዦች በተገኙበት ተካሂዷል።
የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እየተከናወነ የሚገኘውን ሥራ አስመልክቶም የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሌና የአፋር ክልል የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊዎች ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ወጥ የኾነ ጸጥታ መዋቅር እንዲኖር ለማድረግ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የሚያስችል ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።
ወጥ የኾነ ሀገራዊ የጸጥታና ደህንነት ኀይል እንዲኖር በማድረግ ልዩ ኀይሉን መልሶ ለማደራጀት በክልሎች መካከል መተማመን መደረሱንም ተናግረዋል።
ልዩ ኃይሎች የሀገርን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታሪክ የማይዘነጋው አኩሪ ድል መኾኑን አንስተዋል።
ልዩ ኀይሉን መልሶ ለማደራጀት እየተካሄደ የሚገኘው ሥራም በጥናት ላይ የተመሰረተና የሀገርን ዘላቂ ሰላም ማስቀጠል የሚያስችል ጸጥታ መዋቅር ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሁሉም ዜጎች እምነት የሚያሳድሩበት የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት የመልሶ ማደራጀት ተግባሩ አስፈላጊ ኾኖ መገኘቱን አስታውቀዋል።
በሕገ-መንግሥቱም ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ፌደራል ፖሊስና የክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲኖር የተደነገገ መኾኑን አንስተው የልዩ ኀይል አደረጃጀት ግን ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየቱን ተናግረዋል።
የመለዮ ለባሽ መብዛት አንዱ የሌላውን ኃላፊነት በመጋፋት ዜጎች በእኩል አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግ በጸጥታ ሥራው ላይ እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸዋል።
በክልል ልዩ ኀይሎች ላይ እየተደረገ ያለው የመልሶ ማደራጀት ሥራም “ለተወለድኩበት ብሔር ነው የቆምኩት የሚለውን እሳቤ በማስተካከል” ኢትዮጵያውያን በእኩል የሚተማመኑበት የጸጥታ አካል ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ልዩ ኀይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራው መጠራጠርን በማስቀረት ዜጎች የሚተማመኑበትን ኀይል ለመገንባት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ በበኩላቸው የልዩ ኀይል አባላት እንደ የፍላጎታቸው መከላከያ ሠራዊቱን፣ ፌዴራል ፖሊስን እንዲሁም በመደበኛ ፖሊስን እንዲቀላቀሉ መደረጉ ሕዝቡን የበለጠ ለማገልገል እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ውሳኔው ሰፊ ውይይት የተደረገበት መኾኑን የሚናገሩት ደግሞ የሶማሌ ክልል ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ኀላፊ ጦይብ አሕመድ ልዩ ኀይሉን መልሶ በማደራጀት ሕጋዊ መልክ የማስያዝ ሥራው ጉልህ ሀገራዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ዲኒ፤ መልሶ የማደራጀት ሥራው የልዩ ኀይሉን አባላት መብትና ጥቅም ባከበረ መንገድ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።
በተለያዩ አካላት “ልዩ ኀይሉ ሊበተን ነው፤ ሊፈርስ ነው፤ ትጥቅ ሊፈታ ነው” በሚል የሚነዛው አሉባልታም ትክክል እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የመልሶ ማደራጀት ተግባሩም የልዩ ኀይል አባላት እንደ ፍላጎታቸው መከላከያ ሠራዊትን፣ ፌደራል ፖሊስን እንዲሁም መደበኛ ፖሊስን ተቀላቅለው የሀገርን ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቁበት እድል መመቻቸቱን ተናግረዋል።
በአደረጃጀቱ ፈቃደኛ ሳይሆን ወደ መደበኛ ሕይወቴ እመለሳለሁ የሚል የልዩ ኃይል አባል ካለም ድጋፍ ተደርጎለት ማኅበራዊ ሕይወቱን እንዲቀጥል ይደረጋልም ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዳሉት መልሶ የማደራጀት ሥራው ለሕዝብ አገልግሎት መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩ የልዩ ኃይል አባላትን ለተጨማሪ ተልእኮ ከማዘጋጀት ያለፈ ዓላማ የለውም ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ የልዩ ኀይል አባላት ለማደራጃት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ውይይት አድርገን መግባባት ላይ ደርሰናል ወደ ሥራ እየገባን ነው ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ ጦይብ አሕመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤መልሶ የማደራጀት ሥራው ትጥቅ የማስፈታት ዓላማ የለውም።
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ዳኒ የልዩ ኃይል አባላት እንደ የፍላጎታቸው የጸጥታ ኃይሉን ተቀላቅለው በቅርቡ ኅብረተሰቡን ለማገልገል መልሶ ማደራጀት ሥራው ሰፊ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።
የመልሶ ማደራጀት ሥራውም ዜጎችን በእኩልነት ማገልገል የሚችል የጸጥታ ተቋም እንዲኖር ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሆኑን ኢትዮጵያዊያን ሊገነዘቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡም ለሚነዙ አሉባልታዎች ጆሮ ባለመስጠት የመልሶ ማደራጀት ተግባሩ ለበጠ ሀገራዊ ሰላምና ደህንነት ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን መረዳት እንዳለበት ገልጸዋል።
በመልሶ ማደራጀት ተግባሩም የልዩ ኃይል አባላት ሥልጠና ወስደው በተዘጋጁ የጸጥታ አደረጃጀቶች መዋቅሮች እንደየፍላጎታቸው መግባት እንደሚችሉም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደ የሙያቸው ሥልጠና ይወስዳል፤ ከዚያም ፍላጎትን መሰረት በማድረግ በኋላ ወደ ተለያዩ የጸጥታ ዘርፍ መዋቅሮች ውስጥ ይገባሉ ብለዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ ሕዝቡ ሰላም አግኝቶ ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ በመሆኑ ሕዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የሶማሌ ክልል ጸጥታ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ ጦይብ አሕመድ ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላም ነው፤ አሁን ላይ እየተደረገ ያለውን ይህንን ለማጽናት ነው።
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ዳኒ ልዩ ኃይል ሕጋዊ መሰረት ስለሌለው ወደ ሕጋዊ ተቋም መልሰን ለማደራጀት ያለመ ነው ብለዋል።
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅ እንጂ ትጥቅ የማስፈታትና የመበተን ዓላማ እንደሌለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫም፤ ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራው ወጥ የኾነ ጠንካራ ሀገራዊ የጸጥታ ኃይል መገንባትን ዓላማው ያደረገ መኾኑን መግለጻቸውም እንዲሁ።
የልዩ ኃይል አባላቱ ሦስት አማራጮች አሏቸው፤ የመጀመሪያው ወደ መከላከያ ሠራዊት መቀላቀል፣ ሁለተኛው ደግሞ ባሉበት ክልል የፖሊስ ኃይል መግባት እንዲሁም ወደ መደበኛ ኑሮ መመለስ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!