
ገንዳውኃ፡ መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው እምቅ ሃብት አኳያ የዞኑ መቀመጫ ገንዳውኃ ከተማ ከሱዳን በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ መገኘቷና ኢትዮ- ሱዳንን የሚያገናኘው ዋና መንገድ የሚያልፍባት ከተማ መኾኗ ለልማት ተመራጭ አድርጓታል፡፡
ከተማዋ የልማት ማዕከል ብትኾንም በመሠረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት የከተማዋ እድገት ተገድቦ መቆየቱን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ካነጋገርናቸው ውስጥ አቶ ደሳለኝ ደምሴ እንዳሉት ከዚህ በፊት በክረምት ወቅት በሚከሰተው ጎርፍና ጭቃ ነፍሰጡር እናቶችንና የታመመን ሰው ፈጥኖ ሕክምና ለማድረስም ኾነ ሌሎች ችግሮች በሚያጋጥምበት ጊዜ ቀድሞ ለመድረስ ይቸገሩ ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ በሚሠሩ የመንገድ ሥራዎች በበጋ ወቅት የሚነሳውን አቧራ፣ በክረምት ደግሞ የሚከሰተውን ጎርፍና ጭቃ መቅረፍ ተችሏል።
ከተማ አሥተዳደሩ የተጀመሩ ሥራዎችን በወቅቱ በማጠናቀቅ ለትራንስፖርት ክፍት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የከተማው ሌላው ነዋሪ ጡሃ መሃመድ እንዳሉት ደግሞ አካባቢው ሜዳማ እንደመኾኑ በክረምት ወቅት በሚፈጠር የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ነዋሪዎች ላይ መፈናቀል ሲያስከትል ቆይቷል።
አሁን የሚሠራው የመንገድ ሥራ ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም በቀጣይ በከተማው በሚከናወኑ መሠረተ ልማቶች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የገንዳወኃ ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አካሌ ማዘንጊያ እንዳሉት በ2015 ዓ.ም በከተማ አሥተዳደሩ 23 የአዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታና የነባር ፕሮጀክቶች ጥገና ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አረንጓዴ ልማት፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ ጠጠር መንገድ፣ የውኃ ማፋሰሻ ሥራ፣ የወጣቶች መዝናኛና የትምህርት ቤት ግንባታዎች ይገኙበታል።
በ2015 ዓ.ም ከዓለም ባንክ፣ ከመደበኛ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና ከማኅበረሰቡ በተሰበሰበ 91 ሚሊዮን ብር በከተማ አስተዳደሩ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ በማሳያነት አንስተዋል። ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ የጌጠኛ ድንጋይ ማንጠፍ የተጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። እስከ አሁንም ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ሥራ መሥራት መቻሉን አስረድተዋል።
አካባቢው ሜዳማና ጥቁር አፈር የሚበዛበት በመኾኑ ማኅበረሰቡ በክረምት ወቅት ለጎርፍና ለተለያዩ ለችግሮች ይጋለጥ እንደነበር ነው ኀላፊው ያነሱት።
ሌላኛው የከተማዋ ትኩረት ደግሞ አረንጓዴ ልማት ነው። በተሰጠው ትኩረትም አካባቢው ልምላሜውን ባጣበት በዚህ ወቅት ከተማዋ በልምላሜ ደምቃ እንድትቀጥል ተደርጓል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!