አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ተጠቃሚዎች በማድረስ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መቀነስ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ፡፡

87
ባሕርዳር: መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና በባሕርዳር ዳር ዙሪያ በሚገኙ ኮሌጆች መካካል የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የተግባር ጥናት እና ምርምር እንዲሁም የፈጠራ ሥራ ውድድር እየተካሄደ ነው፡፡
ተወዳዳሪዎቹ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ይዘው ቀርበዋል፡፡ የፈጠራ ውጤቶቹ በዳኞች ተገምግመው ለቀጣይ ክልል እና ሀገር አቀፍ ውድድሮች እንዲዘጋጁ ማስተካካያ ተሠጥቷቸዋል፡፡
የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች በቦታው ተገኝተው የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶችን ተመልክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አማረ አለሙ የፈጠራ ተግባራትን በማበረታታት ከውጭ የሚመጣውን ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መተካት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚሸጋገሩ ባለሃብቶችን ማፍራትና ቴክኖሎጅዎችን በማስተዋወቅ አምራቹን ከተጣሚው ጋር በማገናኘት የገበያ ትሥሥር መፍጠር እንደሚገባም አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡
የክህሎት፣ የቴክኖሎጅ፣ የተግባር ጥናት እና ምርምር የፈጠራ ሥራ ውድድር በክልል ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ በፌዴራል ደረጃ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ የሚወዳደሩ ሰዎችን ለመለየት የሚካሄድ ነው፡፡
በአማራ ክልል እስካሁን በተካሄዱ ውድድሮች ለአርሶ አደሮች፣ ለባለሃብቶች የሚጠቅሙ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች የተለያዩ ድርጅቶች እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡ ይህም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች የአካባቢውን ችግር የሚፈቱ፣ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያላቸው፣ አካባቢን የማይበክሉና ወደ ተጠቃሚው ሲወርዱ በቀላሉ መጠቀም የሚቻል መኾን እንዳለባቸው ምክትል ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
በውድድሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እና አቅራቢዎችንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም በበጀት ለመደገፍ መታቀዱንም አቶ አማረ አስረድተዋል፡፡
የባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ፈለቀ ውቤ ውድድሩ በኮሌጅ፣ በክላስተር፣ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡ ውድድሩ ተወዳዳሪዎችን ያበረታታል፣ ተወዳዳሪዎቹም የሚያዘጋጁት ነገር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው፣አስፈላጊነቱ እና አካባቢን የማይበክል መኾኑ መረጋጋጥ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
እነዚህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ግብዓት ተሟልቶላቸው ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ የሚደረጉ ውድድሮች ለማሳያ ብቻ ኾነው እንዳይቀሩ ክልል ግብዓት ማቅረብ አለበት ነው ያሉት፡፡
ብረት ሳይቆራረጥ ወደ ክብነት የሚቀይር ማሽን የሠሩት መምህር ዳዊት ደሴ የሠሩት ማሽን ጊዜን ጉልበትን እና ወጪን የሚቆጥብ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ካሁን በፊት በዚህ ልክ የተሠራ ባይኖርም ብረት የሚሠሩ ሰዎችን ችግር አይተው እንደሠሩት ነግረውናል፡፡ ተገቢው ድጋፍ የሚደረግላቸው ከኾነ ለበርካታ ሰዎች መሥራት እንደሚችሉ አስረድተዋል ቴክኖሎጅው እንዲሥፋፋ እና በርካቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
በባሕር ላይ አገልግሎት የምትሰጥ ብስክሌት የሠራው ተወዳዳሪ ተማሪ ይታያል አምባነህ በበኩሉ ጎብኝዎች ያለምንም ችግር በባሕር ላይ እንዲንቀሳቀሱ እና እንዲዝናኑ ይረዳል ብሎናል፡፡ ቴክኖሎጅው በቀላል ወጪ የሚሠራ በመኾኑ ማዘጋጀት እና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም ተናግሯል፡፡ የፈጠራ ሥራው ከማዝናናት በተጨማሪ ለዓሣ አስጋሪዎች እና ሥራቸውን በባሕር ላይ ላደረጉ ሰዎችም ትልቅ አገልግሎት እንደሚሠጥ ነግሮናል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከ87 ሺህ በላይ የመማሪያ መጽሐፍት ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ድጋፍ ተደረገ።
Next articleበማኅበረሰቡ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሠራ እንደሚገኝ የገንዳውኃ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።