
ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው በበጀት ዓመቱ ከ42 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ ነበር፡፡
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አግማስ ጫኔ ክልሉ ባለፉት ሥምንት ወራት ከተለያዩ የግብር አርስቶች ከ25 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰበት በመኾኑ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማት፣ ጤና ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶች የወደሙበት፣ የመድኃኒት አቅርቦት በሠፊው የሚያስፈልግበት፣ በርካታ ሥራ ፈላጊዎች ያሉበት ክልል በመኾኑ ገቢን መሠብሠብ ቅድሚያ የሚሠጠው ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል፡፡
አቶ አጉማስ ለመሰብሰብ የታቀደው ገቢ የክልልን የበጀት ፍላጎት በ45 በመቶ እንደሚሸፍንም አንስተዋል፡፡
የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 8 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡
ወልድያ ከተማ፣ ደብረታቦር ከተማ፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ወሎ ዞን የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ሲኾን ደሴ ከተማ፣ ምዕራብ ጎንደር ዞን፣ ጎንደር ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
ከቤት ኪራይ ገቢ፣ ከግል ተቀጣሪዎች፣ ከንግድ ትርፍ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከደላላዎች፣ ከተርን ኦቨር ታክስ የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸው የገቢ አርዕስቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡
አቶ አግማስ እንዳሉት የእርሻ ገቢ ግብር እና ከፋብሪካዎች የሚሰበሰብ(ኤክሳይዝ) ግብር ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው አርዕስቶች መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡
ሕገወጥ ንግድ፣ በደላላ የሚመራ ንግድ፣ ስውር ንግድ፣ ሀሰተኛ ደረሰኝ የመሳሰሉ አሠራሮች መንግሥት ተገቢውን ገቢ እንዳያገኝ አለፍ ሲልም ከካዝና የሚወስዱ ሕገወጦች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
የሥነ ምግባር ጉድለትና የመረጃ ሥርዓት አለመኖር ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን ግብር ለመንግሥት እንዳያስገባ እንደሚያደርግም አቶ አግማስ አስረድተዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ደረሰኝ እንዲጠይቅ፣ ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ፣ ለግብር ሕግ ተገዥ እንዲኾን በየአካባቢው ትምህርት እየተሠጠ ነውም ብለዋል፡፡ ሕጉን በሚተላለፉ አካላት ላይ ቢሮው አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ አግማስ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ አዲስ የሚጀመሩትንም ለማስፈጸም ቀሪውን 18 ቢሊየን ብር መሠብሠብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ከ340 ሺህ በላይ ነጋዴዎች አሉ፣ ከዚህ ውስጥ ከ18 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ ከእነዚህ ተመዝጋቢዎች 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደ ሲኾን እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወይም 60 በመቶ ያህሉ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
አቶ አግማስ የኑሮ ውድነትን፣ የመሠረተ ልማት ጥያቄንና የሥራ አጥነት ጥያቄን ለመመለስ ግብር ከፋዩ ግብር መክፈል አለበት ነው ያሉት፡፡ መንግሥትም የተሰበሰበውን ግብር ለልማት በማዋል ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ግብር ከፋዮችም የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈ ተጠቃሚዎቹም ደረሰኝ በመጠየቅና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥሙ ለሚመለከተው አካል በመጠቆም የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ዘመናዊነትን የተከተለ የግብር አከፋፈል ሥርዓት ለመዘርጋት እና የሕዝቡን የልማት ጥያቄ የሚመልስ ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችል አሠራር ለመጀመር ማቀዱንም አቶ አግማስ አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!