
አዲስ አበባ:መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር እና የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ የዓለም ጤና ቀንን ”ጤና ለሁሉም” በሚል መሪ ሀሳብ በፓናል ውይይት እያከበሩ ነው።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚንስትር ዴኤታ አየለ ተሾመ (ዶ.ር) በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኮቪድ 19 ፣ በድርቅ እና በግጭት ምክንያት እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዓላማ የሆነውን ቅድመ መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያ በተለይ ወረርሽኝን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ መቻሏን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለውጥ ፣በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ምክንያቶች የጤና አገልግሎት የማያገኙ ዜጎችን መፍትሔ ለማምጣት ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በጋራ እንደሚሠራ ሚንስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ጤና ለሁሉም በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም ጤና ቀን የድርጅቱ 75ኛ የምስረታ ዓመት በሚከበርበት ጊዜ መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዲላሚኒ ኖንሃላናሃላ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡ ተወካዩ በኢትዮጵያ ባለፉት 75 ዓመታት በተለይ በወሊድ ወቅት የእናቶችን ሞት እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።
በቀጣይ በድርቅ ፣በግጭት እና መሰል ምክንያቶች እየተከሰተ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የዓለም የጤና ድርጅት ድርሻውን እንደሚወጣ ዶክተር ዲላሚኒ ገልጸዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት እና የዓለም የጤና ቀንን ምክንያት በማድረግ ”ጤና ለሁሉም ” በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
ዘጋቢ፡- ዳንኤል መላኩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!