
ባሕር ዳር:መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ አማራ የሚቲዎሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል የሚቲዎሮሎጅ ባለሙያው መልካሙ በላይ ለአሚኮ እንደተናገሩት፣ አሁን ላይ ባለው የአየር ትንበያ መረጃ መሰረት በአማራ ክልል በልግ አብቃይ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እያገኙ ነው።
በተለይም በመጋቢትና በሚያዚያ ምሥራቅ አማራ፣ ከደሴ ዙሪያ እስከ ሰቆጣና ራያ አካባቢዎች በበልግ ወቅት ዝናብ አምራች ናቸው ።የበልግ ወቅት ዝናብ ትንበያው ተለዋዋጭ እንደኾነ የሚናገሩት ባለሙያው በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከፍተኛ ዝናብ እየተመዘገበ እንደኾነ ነው የሚናገሩት።
የትንበያ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቀጣዩቹ 10 ቀናት የበልግ ዝናቡ ተስፋፍቶ ይቀጥላል ብለዋል። በቀጣይ ሚያዚያ ወርም ከመደበኛው በላይ ከ60 እስከ 80 በመቶ የበልግ ወቅት ዝናብ እንደሚኖር የአየር ትንበያው ያሳያል ነው ያሉት ባለሙያው።
ዝናቡ የበልግ ወቅትን ተጠቅመው ከሚያመርቱ አካባቢዎች ባሻገርም ወደ ሌሎች ምዕራብ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው ብለዋል። ይህም ለክረምት ወቅት አዝመራ ለእርሻ ዝግጅት የሚኾን ጠቃሚ ዝናብ እንዳለ ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!