“የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

63
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥቷል።
አዲስ አበባ :መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መግለጫውን የሰጡት ሚንስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሣ በፀጥታ እና የልማት ጉዳይ ላይ ነው መግለጫ የሰጡት መንግሥት ሪፎርም ከሠራባቸው ዘርፎች አንዱ መከላከያ ሰራዊት ነው ለውጡም የሚታይ ነው ያለጠንካራ መከላከያ ሰራዊት ሀገር መገንባት አይቻልም እና ቅድሚያ ተሰጥቶት በጥናት ተመስርቶ ተስርቷል ። በዚህ መሠረት የየክልሉን ልዩ ኀይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል። ሀገራዊ ሰላምን ለማስጠበቅ ኀላፊነት ያለበት መንግሥት በተለያዩ ከሕዝቡ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ማለትም አንድ ጠንካራ በሁሉም ነገር የተደራጀ ሰራዊት መፍጠር የሚል በብዙ አካባቢ ሲነሳ ነበር ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
በዚህ ሐሳብ ላይም ከልዩ ኀይል አመራሮችና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ ተደርሷል። ቀደም ብሎም በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ በተገኘው ውጤትም ያለምንም ልዩነት ውሳኔው ስምምነት ተደርሶበታል ። ይህ ተግባር እንዲፈፀም መላ ሕዝባችንም ሲጠይቅ ቆይቷል። ይሄንን ተከትሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ነው ያሉት።
ልዩ ኀይሎች ለሀገራቸው መስዋትነት በመክፈላችው መንግሥት ዕውቅና ይሰጣል ብለዋል፡፡ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኀይል አባላት እንደ ምርጫቸውና እንደ ፍላጎታቸው በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት ይችላሉ፣ ለዚህም ሦስት አማራጭ ተዘጋጅቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የመጀመሪያው መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀል ሁለተኛው ክልሎችን እና ሕዝብን ለማገልገል በፓሊስ ኀይል መግባትና ሶስተኛው አማራጭ ወደ ሲቪል ህይወት ለመመለስ ለፈለገ አስፈላጊው ነገር ተደርጎ እንዲመለስ ውይይቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ይሄንን በመረዳትም በሁሉም ክልሎች ሂደቱ በመግባባትና በውይይት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
ነገር ግን በመረጃ እጥረት እና ሌሎች ምክንያቶች ብዥታ ሲፈጠር ታይቷል። ይሄንን ደግሞ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት እና በሁሉም አካባቢ የሚከናወን መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ጉዳዩ ከትጥቅ ማስፈታት ጋር የሚገናኝ ነገር የለውም የሚሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ አንድነትን የሚያሳየውን መከላከያን ማጠናከር እና አንድነትን ከማምጣት አንፃር የተሠራ መሆኑን ማስረዳት እንፈልጋለን ብለዋል።
በሌላ በኩል ሕወሐት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑ ሊታወቅ ይገባልም ብለዋል። የሕወሐት ትጥቅ የመፍታት ሂደት በተፈረመው ስምምነት መሠረት ያለማወላወል የሚፈጸም እንጂ ከሌላ ሀገራዊ ዕቅድ ጋር የሚቀናጅም የሚጣረስም አይደለም። ይሄንንም የሚከታተል ቡድን እንዳለም አስረድተዋል፡፡
ዓላማው ትልቋን ኢትዬጵያ እና እሷን የሚመጥን ለሁሉም የሆነ አንድ ኀይል ከመፍጠር አንፃር ብቻ መሆኑን በመረዳት እና በሁሉም ቦታ እኩል የሚፈጸም መሆኑን በመረዳት ከዚህ ውጭ የሚነሱ የሃሰት መረጃዎችን መከላከል እና አብሮ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
በሸኔ ጉዳይ በርካታ በሽብር ቡድኑ ስር የነበሩ ቦታዎች ነፃ ወጥተው መደበኛ እንቅስቃዎችን ለማስጀመር ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በተዘረጋው የሰላም ጥሪም በርካታ የቡድኑ አባላት ወደ ሰላሙ እየመጡ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት በዚህ ዙሪያ ለሚሠሩ ምስጋና እያቀረበ አሁንም ለሸኔ እና በሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ ኀይሎች ሁሉ ለሰላም በሩ ክፍት ነው ብለዋል ።
ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ መንግሥት የቀበሌ መዋቅሮችን በማጠናከር ያምናል እናም አቅማቸውን የመገንባት ሥራ እየተተገበረ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ ለምሳሌ 635 ሺህ በላይ የሚሆኑ በኦሮሚያ አካባቢ በቀበሌ ለሚገኙ የፀጥታ እና የልማት መዋቅሮች ስልጠና እየተሰጠ ነው ይሄ በሌሎች አካባቢዎችም ይሄው ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የህገወጥ ንግድ እና የንግድ አሻጥሮች ከሀገር የተሻገረ ዓለም አቀፍ ትስስር ያለው ነው እናም ይህን ለመከላከል ሥራዎች ሲሠሩ ነበር በዚህም በሕገወጥ መንገድ የማእድን ማውጣት እና ማምረት ሥራ ላይ የነበሩ በሁለት ክልሎች በቤንሻጉል ጉምዝ እና በጋንቤላ ክልል 92 የውጭ ሀገር ዜጎች እና 12 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል።
ይህ የሆነው ሰላም በመሆኑ እና መንግሥት ትኩረቱን ወደ ልማት ያዞረ በመሆኑ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ግለሰቦቹንም በክትትል ከነኤግዚቢታቸው መያዝ ስለመቻሉም አስረድተዋል። በሥራው ላይ የሕዝቡ ርብርብ እና ተሳትፎ ሰፊ ነበር ያሉት ሚንስትር ዴኤታዋ አሁንም መንግሥት የሚሠራው ሥራ በሁሉም ክልል ያለ ተግባር በመሆኑ ኅብረተሰቡ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ሚኒስትር ዴኤታዋ በበልግ እርሻ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት በማረስ 24 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታሰቡን አስረድተዋል። ሌላው 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ከከረመው 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ለማስራጨት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል እስካሁን መሰራጨቱንም አስረድተዋል።
የበልግ ዝናቡን በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጅት ማድረግ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የደረሱ ሰብሎች በዝናብ እንዳይበላሹ ርብርብ በማድረግ መሰብሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- አብነት አስከዚያ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየ2015/16 የምርት ዘመንን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡
Next article“በአማራ ክልል በልግ አብቃይ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እያገኙ ነው” የምዕራብ አማራ የሚቲዎሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል