የ2015/16 የምርት ዘመንን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

44
ደሴ:መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተዘጋጀው የሰብል ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የኤክስቴንሽን የአስልጣኞች ሥልጠና በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በሥልጠና መርሐ ግብሩ የባለፈው ዓመት የምርት ዘመን ጥንካሬዎችና ድክመቶች ተነስተው መግባባት ላይ ይደረስባቸዋልም ነው የተባለው፡፡
የግብርና ቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ባለፈው ዓመት 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት በቅድመ ትንበያው 140 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደተገኘ አመላክተዋል፡፡
በዘንድሮው የምርት ዘመን ደግሞ በ5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ150 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው ዕቅዱን ለማሳካት ከስልጠናዎች ባሻገር አስፈላጊ የቴክኖሎጅ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል። ሰፋፊ መሬቶችን ወደ ሜካናይዜሽን ማስገባት፣ በዋና ዋና ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትና የሚታዩ ክፍተቶችን በየጊዜው መፍታት በዋናነት የሚሠራባቸው ጉዳዮች ስለመሆናቸው አስገንዝበዋል፡፡
ክልሉ ሙሉ እቅሙን በመጠቀም ምርትን በስፋት ለማምረት በቅንጅትና በመግባባት ይፈጸማል ነው ያሉት።
ያነጋገርናቸው የሥልጠናው ተሳታፊዎች በዘርፉ የሚስተዋሉ የአስተሳስብ ክፍተቶች በሥልጠናው እንደሚሞሉ ተስፋ አድርገዋል። በአስልጣኞች ስልጠናው የምሥራቅ አማራ ዞኖች ከተማ አሥተዳደሮችና ወረዳዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየፈተና ውጤት ማስታወቄያ
Next article“የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ ነው” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት