የኦክጅን እጥረቱ በመጠኑ መቃለሉን አብመድ ያነጋገራቸው በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት ገለጹ፡፡

187

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ስድስት የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከላት አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ በአማራ ክልል ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ የሕክምና ኦክስጅን አቅርቦቱ ከ20 በመቶ በታች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ከስምንት ወራት በፊት የባሕር ዳር ሕክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ሲከፈት ችግሩን በተወሰነ መጠን እንደሚያቃልል ታምኖበት ነው፡፡ አብመድ አሁን ላይ የሕክምና ኦክስጅን አቅርቦት በክልሉ ምን እንደሚመስል መለስ ብሎ ቃኝቷል፡፡

በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዐብይ ፍሰሃ እንደተናገሩት አማራ ክልል ምንም ዓይነት የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ ባልነበረበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ይመጣ አንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ወደኋላ መለስ ብለው ሲያስታውሱም በ2008 ዓ.ም በሀገሪቱ ግጭትና አለመረጋጋት ሲቀሰቀስ ኦክስጅን በመዘግየቱ ምክንያት 40 የሚሆኑ ሕጻናት ሕይወታቸው ማለፉን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በዚህ ወቅት ግን የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቆራረጥ ካልሆነ በቀር በአቅራቢያ የባሕር ዳር ሕክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል በመከፈቱ ችግራችን ተፈቷል ባንልም ተቃሏል፣ ታካሚዎች በቀን ከ100 በላይ ሲሊንደር እየተጠቀሙ ነው›› ብለዋል። በሆስፒታሉ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ‹ነርስ› ሀብቴ ብርቁ ደግሞ ‹‹ከስድስት ወራት በፊት እንደነበረው ሳይሆን በተፈለገው ጊዜ ሳይጠየቅ ይቀርባል›› ሲሉ በሕክምና ኦክስጅን አቅርቦት በኩል የመጣውን መሻሻል ገልጸዋል፡፡

‹‹ከአዲስ አበባ በግዢ ስለምናመጣ በፀጥታ ችግርና ከባድ ተሽከርካሪዎች ቀን መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ችግሮች አጋጥመው ነበር›› በማለት የቀደመውን ችግር ያስታወሱት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ዋና ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ናቸው፡፡ በሆስፒታሉ ከሁለት እስከ ሥስት ቀናት 170 ሲሊንደር የሕክምና ኦክስጅን ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተናግረዋል፡፡ ፍላጎቱ ከታካሚው ጋር ሲነፃፀር ግን በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአማራጭነት ጥቂት ኦክስጅን ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ኦክስጅን “ኮንሰንትሬተር” እየተጠቀሙም ነው፤ የባሕር ዳሩ ኦክስጅን ማምረቻና መከፋፈያ ማዕከል መዘግዬትና መስተጓጎሉን የሚያስቀር ቢሆንም በአቅራቢያ የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል ቢከፈት ችግሩ ይበልጥ እንደሚቃለልም አመልክተዋ፡፡
የደብረ ብርሃን ሆስፒታል ተወካይ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፅጌ ታየ ደግሞ ‹‹ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንገድ እየተዘጋ የሕክምና ኦክስጅን ከአዲስ አበባ ማምጣት አስቸጋሪ ሆኗል›› ነው ያሉት፡፡ 2011 ዓ.ም 9 ሺህ ተኝተው የሚታከሙ እና 19 ሺህ የሚጠጉ ድንገተኛ ታካሚዎች የሕክምና ኦክስጅን መጠቀማቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ከ70 እስከ 80 ሲሊንደር በሦስት ወይም አራት ቀናት ልዩነት አንድ ጊዜ እንዲቀርብ ውል ተይዞ እየተሠራ ነው፤ በተለይ የሕክምና ኦክስጅን ዕርዳታ የሚጠይቁ ጤና ተቋማት በርካታ በመሆናቸው ሰሜን ሸዋ ላይ አንድ ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ቢከፈት መልካም ነው›› ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ሕክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ የሺዋስ አንዷለም ማዕከሉ ማምረት በጀመረበት ስምንት ወራት ውስጥ ፈለገሕይወት ጠቅላላ ሆስፒታል በወር ለሕክምና ኦክስጅን ያወጣ የነበረውን 1 ሚሊዮን ብር ወጪ ማዳኑን፤ የጤና ተቋሙ አሁን ከ60 እስከ 72 ሲሊንደር እየተጠመቀ መሆኑንና በክልሉ ያሉ ከ80 በላይ ሆስፒታሎች ፍላጎት ግን ማሟላት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ ከባሕር ዳር ውጭ ከተማው ውጭ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሠላም፣ ጎንደር፣ ሳይንት፣ ነፋስ መውጫ፣ እንጅባራ … ተራቸውን ጠብቀው የሕክምና ኦክስጅን ምርቶችን ይወስዳሉ፡፡ ‹‹የመብራት መቆራረጥና የማምረቻ ማዕከሉ መሳሪያ ገመዶች ሲሊንደር ጋር ያለመግጠም ችግር ቢኖርም በቀን 120 ሲሊንደር በማምረት በሙሉ አቅም እየሠራ ነው›› ብለውናል፡፡

የባሕር ዳሩ ሕክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ማምረት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካለፈው ሳምንት ድረስ 13 ሺህ 480 ሲሊንደር ማምረቱን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ደበበ ገልፀዋል፡፡ ማዕከሉ በክልሉ አቅራቢያ ለሚገኙ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን እየሰጠ ቢሆንም ለሙሉ ጤና ተቋማት ግን አገልግሎቱን እያዳረሰ ነው ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥታዊ ያልሆኑና የሌሎች አካላትን ትብብር እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ ትልልቅ ሪፌራልና ጠቅላላ ሆስፒታሎች ባሉባቸው አካባቢዎች ‹‹መቼ ይፈፀማል›› የሚለው ባይታወቅም የሕክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከላት ለመገንባት እንደታሰበም ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

ከአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የደሴ ሕክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ አይደለም፤ የግብዓት ችግሮችም አሉበት፡፡ ማምረቻው በቀን ከ70 እስከ 100 ሰሊንደር እንደሚያመርትም ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Previous articleበምሥራቅ አማራ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ጥረቱ ቢቀጥልም ምንጩ ላይ መቆጣጠር አለመቻሉ አደገኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለ66 ፕሮጀክቶች ማስጠንቀቂያ ሰጠ፤ 34 ፕሮጀክቶችን ደግሞ ቦታ ነጠቀ፡፡