የውጭ ምንዛሬ ለቡሬ ኤሌክትሪክ ኀይል ፕሮጄክት ግንባታ ፈተና ኾኗል።

183
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቡሬ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክና ሌሎች ፋብሪካዎችን የኤልክትሪክ ኀይል ጥያቄ ይፈታል የተባለለት የሰብስቴሽን ግንባታ የውጭ ምንዛሬ ፈትኖታል፡፡

ቡሬ የበርካታ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሆነች ከተማ ናት፡፡ በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ የሚገቡ ባለሃብቶች የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ችግር እየገጠማቸው መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በቡሬ የተገነባው የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክም የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ይፈልጋል፡፡

ለፓርኩና ለሌሎች ፋብሪካዎች የኤሌክትሪክ ኀይል ጥያቄ ለመመለስ የሰብስቴሽን ግንባታ በቡሬ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ግንባታው በ18 ወራት ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተባለለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡

ግንባታው የተጀመረው የፓርኩ የኤክትሪክ ኀይል አቅርቦት ፕሮጄክቱ 230 ኬ ቪ ነው፡፡ ፕሮጄክቱ ሲጠናቀቅ ለቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተረጋጋ እና አስተማማኝ የኀይል አቅርቦት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ፕሮጄክት ሳይት ማናጀር ጆኒ ሺ ከፕሮጄክቱ ሁሉም ሥራዎች 15 በመቶ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጄክቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እየፈተነው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬው እጥረት ከተፈታ በተባለለት ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ባለበት ከዘገየ ግን ተጫማሪ ጊዜያትን እንደሚፈልጉ ነው የተናገሩት፡፡

ፕሮጄክቱ ትልቁ ጥያቄ የኤል ሲ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የቡሬ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሥራ አስኪያጅ ዳኛቸው አሥረስ በ2015 ዓ.ም ፓርኩ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኀይል ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በፕሮጄክት ግንባታው ያጋጣሙ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 230 ኬቪ የሚሸከመውን ፕሮጄክት ችግር ለመፍታት የክልል እና የፌዴራል መንግሥት በትኩረት እየሠሩበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ የውጭ ምንዛሬ (ኤል ሲ) ጉዳይ ባለመፈታቱ ሥራው በተፈለገው ልክ መሄድ አልቻለም ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬውን ጉዳይ ለማስፈታት ከብሔራዊ ባንክ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ችግሩ አልተፈታም ነው ያሉት፡፡ ትልቁ ማነቆውም ኤል ሲውን ማስከፈት ነው ብለዋል፡፡

ከንግድ ባንክ ብድር መፈጸማቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የብር ችግር የለብንም፣ ከውጭ የሚመጣውን እቃ ለማስገባት ግን ኤል ሲ መከፈት አለበት ነው ያሉት፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ግፊት እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬው ችግር ከተፈታ ሥራው እንደሚፈጥንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስፖርት ዜና ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ)
Next articleቺርቤዋ ሜጋቢት 15 ጌርክ 2015 ምሬት አሜታ