ባሕር ዳር:መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚንስቴር ከሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት፤ ከትምህርት ሚንስቴር እና ከትምህርትና ሥልጠና ባለስልጣን እንዲሁም ከመንግሥት የዩኒቨርስቲዎች ኮንሰርቲየም ጋር በመተባበር የጤናውን ዘርፍ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ለማሳደግ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ለምክክር ቀርበዋል።
በመድረኩም በጤና ሚንስቴር፣ በሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ መካከል ዓለም አቀፍ ብቃት ማረጋገጫ ፈተና (ECFMG/USMLE) በሀገራችን ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ የሦሥትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ሥነሥርዓት ተከናውኗል፡፡ ይህም የጤና ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም ከሀገር ውጪ ለመስራትም ሆነ ለመማር መመዘኛዎችን አጎራባች ሀገራት ሄደው ለመፈተን ከሚደርሰው እንግልት እና ወጪ የሚያድን ነው ተብሏል፡፡
በውይይቱ ለምክክር የቀረበው የሦሥተኛ ወገን የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት የጤና ሚንስቴር፣ ከትምህርት ሚንስቴር እና ከኢትዮጵያ ትምህርት ባለስልጣን ጋር በመሆን የጤና ትምህርት ተቋማት ተዓማኒ፣ ተወዳዳሪ እንዲሁም የሚያስመርቋቸው ባለሙያዎች የተሻለ ብቃት እንዲኖራቸው የሚያስችል እና ተቋማቱም ባለሙያዎቹም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያስችል ሥርዓት መሆኑ ተገልጿል።
በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የጤና ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ፤ ሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል ድጋፍ በማድረግ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን በመደገፍ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅትም አማካሪ ካውንስል በመሆንና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በርካታ ሥራዎችን የሰራ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ስምምነት የተደረሰበት የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በሀገር ውስጥ መጀመር እንግልትን ከመቀነስ ባለፈ የሌሎች ሀገራት ባለሙያዎች ወደ ሀገራችን በመምጣት መፈተን የሚችሉበትና የውጭ ምንዛሬን የሚሳድግ ነው ብለዋል።
በውይይቱ የሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የትምህርት ሚንስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የጤና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን የጤና ሚንስቴር መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!