ባሕር ዳር:መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የገበዘ ማርያም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታው የተጀመረው በ2011 ዓ.ም የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ በሰጠው በጀት ነበር። ግንባታው ይጀመር እንጅ ተጠናቆ አገልግሎት መሥጠት አልጀመረም። በዚህም ነዋሪዎቹ ላልተፈለገ እንግልት መዳረጋቸውን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።አቶ አቻሜ ካሳ በቋሪት ወረዳ የገበዘ ማርያም ነዋሪ ናቸው፡፡
የገበዘ ማርያም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በ2009 ዓ.ም ግንባታው ይጀመር እንጅ ግንባታው ከቆመ ከሦስት ዓመት በላይ እንደኾነው ተናግረዋል፡፡ ለግንባታ ውል የወሰዱ ተቋራጮች ቦታው ላይ አለመኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
አቶ አቻሜ እንደገለጹት በአቅራቢያው ሆስፒታል ባለመኖሩ አገልግሎት ፈላጊዎች 80 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ፍኖተሰላም ከተማ እንደሚሄዱ ተናግረዋል። በዚህም በርካታ ነፍሰጡር እናቶች መንገድ ላይ ሕይወታቸው አልፏል። ጥቂቶች መንገድ ላይ ተገላግለዋል ነው ያሉት። ጥቂቶች በተስፋ መቁረጥ ቤታቸው ተገላግለው በደም መፍሰስ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
የሆስፒታሉ መጠናቀቅ ነዋሪዎችን ከእንግልት እና ከአላስፈላጊ ወጭ ይታደጋል፤ በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል ያለውን ግንኙነትም የሰመረ ያደርገዋል ብለዋል። መንግሥት ጉዳዩን ተመልክቶ ችግሩ በቀላሉ የሚፈታበትን መንገድ እንዲያመቻችም ጠይቀዋል።
ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪው አሥር አለቃ ሙጨው ልመንህ በበኩላቸው ልማት ለተራበው የቋሪት ወረዳ ሕዝብ መንግሥት እንዲደርስ ጠይቀዋል። ሆስፒታሉን ለመገንባት ሲጀመር በሕዝቡ ውስጥ የነበረው ተስፋ ከፍተኛ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ተስፋው ችግር ላይ ወድቋል ነው ያሉት።
በተቋራጮች ችግር ምክንያት የአካባቢው ማኅበረሰብ ጉዳት ማስተናገድ አይገባውም፡፡ ተጠናቆ አገልግሎት መሥጠት እንዲጀምር የሚመለከተው አካል መሥራት አለበት ብለዋል።
የቋሪት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መዝገቡ ውቤ በተደጋጋሚ ክልል ጤና ቢሮ ተገኝተው እንዳመለከቱ አንስተዋል፡፡
ሆስፒታሉ በተጀመረበት ዓመት ጥሩ አፈጻጸም የነበረው ቢኾንም ከተቋረጠ ሦስት ዓመት ሞልቶታል፡፡ በጀት ይለቀቃል ግን የግንባታው ባለቤት እየገነባ አለመኾኑን አንስተዋል፡፡ ሆስፒታሉ ተጠናቆ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሚመለከተው አካል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል ጤና መምሪያ ኀላፊ ደሳለኝ ዳምጤ በዞኑ 53 ሆስፒታሎችን ለመገንባት መጀመሩን እና 23ቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡ ግንባታዎቹ በክልሉ በጀት የሚገነቡ ሲሆን ክትትሉንም የሚሠራው ክልሉ ነው ብለዋል፡፡ የሆስፒታሉ አለመገንባት የመልካም አስተዳዳር ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ በዋጋ ንረት ምክንያት ተቋራጮች በሕዝቡ ላይ መጉላላትን ፈጥረዋል ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሲቪል መሃንዲስ እና የኮንስትራክሽን ዘርፍ አስተባባሪው ተስፋየ አይቸው የቋሪት መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ በሁለት ፌዝ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም የተጀመረው የመጀመሪያው ግንባታ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ቋሪት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሙሉ አገልግሎት እንዲሠጥ ለማድረግ ሁለተኛው ግንባታ በ2011 ዓ.ም ነበር የተጀመረ፡፡ የሆስፒታሉን ሁለተኛ ግንባታ ለማጠናቀቅ 365 ቀን ተይዞለታል፡፡ 68 ሚሊዮን 765 ሺህ 98 ብር ተበጅቶለታል፡፡ የክልሉ የልማት ድርጅት የኾነው የአማራ የመንገድ እና ህንጻ ዲዛይን ማኅበር ይቆጣጠረዋል፡፡ ግንባታው 57 በመቶ ተጠናቋል፡፡ ኢንጅነር ተስፋዬ ተቋራጩ ሥራውን በወቅቱ እንዲያጠናቅቅ በመንግሥት በኩል ድጋፍ ቢደረግለትም ማጠናቀቅ አልቻለም ብለዋል፡፡ መንግሥት ተቋራጩ ግንባታውን እንዲያጠናቅቅ 61 ነጥብ 95 በመቶ የዋጋ ማካካሻ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡
ተቋራጩ ሥራውን በአግባቡ ማጠናቀቅ ካልቻለ ቢሮው ውለታውን አንስቶ ለሌላ ተቋራጭ ለመሥጠት እየተዘጋጀ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ውለታውን ለማንሳት ማስጠንቀቂያ ተሠጥቷቸዋል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ተግባራዊ የማያደርጉ ከኾነ እርምጃው አይቀሬ መኾኑን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!