ፍኖተ ሰላም፡ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በቡሬ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ከ150 በላይ ወገኖች ቋሚ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን አስታውቋል፡፡
መሠረት ነጋሽ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በቡሬ ከተማ ነው፡፡ አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ ድጋፍ የሚያደርግላቸው የቅርብ ዘመድም የላቸውም፡፡ ሕይወታቸው በፈተና የተሞላች ናት፡፡ ድህነት የተጫናቸው፤ ማጣት ያጎበጣቸው ናቸው፡፡
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ምርኩዝ ከኾናቸው አቅመ ደካማ ወገኖች መካከል አንደኛዋ ናቸው፡፡ ግሩፑ ምርኩዝ ኾኗቸው የጎበጠ ሕይወታቸውን እየደገፈ እያኖራቸው መኾኑን ነግረውኛል፡፡
ʺበችግር ስኖር ፈጣሪ ብሎት ድጋፍ መጣልን፡፡ እየመረቅኩኝ፣ ፈጣሪ ይጠብቀው፣ ሀገሩንም ሰላም ያድርገው እያልኩ እየኖርኩ ነው፡፡ ፈጣሪ ብሎልኝ ነው ይሄ እድል የተከፈተልኝ፡፡ በየወሩ ድጋፍ ያደርግልኛል” ነው ያለውናል፡፡
በወር 1 ሺህ 500 ብር እንደሚሰጣቸውም ነግረውናል፡፡ እሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አቅመ ደካሞችንም እየደገፈ መሆኑን ነው የነገሩን፡፡ ሠርተው መብላት ለማይችሉ፣ ጧሪና ቀባሪ ለሌላቸው ሰዎች የክፉ ቀን ሆኗልም ነው ያሉት፡፡
የበላይነህ ክንዴ ግሪፕ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው፤ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ላይ በሥፋት እየተሳተፈ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ግርፑ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በስፖርት እና በምገባ ላይ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በቡሬ ከተማ አሥተዳደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ከ150 በላይ ወገኖች ወርኃዊ ደሞዝ በመመደብ ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ለእያንዳንዳቸው ወገኖች 1 ሺህ 500 ብር ወርኃዊ ተቆራጭ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአቅመ ደካሞችን ቤት አስገንብቶ ማስረከቡንም ገልጸዋል፡፡ በፍኖተ ሰላም ከተማም ለአቅመ ደካሞች ቤት እያስገነባ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ለሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በቀን እስከ 500 ሰው መመገብ የሚችል የምገባ ማእከል ከ15 ሚሊዮን ብር ላይ በሆነ ወጭ ገንብቶ ሥራ ማስጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፉ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ሌሎች ድርጅቶችም በማኅበራዊ ዘርፉ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!