
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ይህን ያለው ለሴቶች፣ ሕጻናት፣ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሥራ አፈጻጸሙን ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
ድርጅቱ የ2011 በጀት ዓመት እና የ2012 ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ለቋሚ ኮሚቴው ዛሬ አቅርቧል፡፡ የድርጅቱን የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የአብመድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ ተቋሙ በተለይም ባለፈው ዓመት በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ተጠምዶ እንደከረመ ገልጸዋል፡፡ ይህም ድርጅቱ የራሱን እቅድ እንዳይሠራ መሰናክል ሆኖበታል ነው ያሉት፡፡ አብመድ በሀገሪቱ የታዬውን ለውጥ በማምጣት በኩል የቀዳሚነቱን ድርሻ እንደሚወስድ ያመላከቱት አቶ ሙሉቀን በክልሉ የሠላምና ደኅንነት ጉዳይ፣ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የመጣው ለውጥ የሕዝብ እንዲሆን ከማድረግ፣ የአማራ ክልል ሕዝቦች እሴቶቻቸውን የሚያዳብሩበትን መንገድ በማሳዬት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የክልሉ የቱሪዝምና ሌሎች ጉዳዮችን በትኩረት እንደሠራም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል፡፡ ድርጅቱ ሃይማኖታዊ በዓላትን፣ ታላላቅ ማኅበራዊ መድረኮችንና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የማገናኘት ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን ስፖርታዊ ክዋኔዎችን የራሱን ወጪ ጭምር በመጠቀም በትኩረት የሠራበት ጊዜ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በአምስት የተለያዩ ቋንቋዎች በተለያዩ ሚዲዬሞች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሆነበት ዓመት እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የመጣውን የዜጎች መፈናቀል ዜጎች ወደቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ሚዲያው የሚጠበቅበትን ሚና እንደተጫወተም አስታውቀዋል፡፡ ቆቦና አካባቢው የነበረውን የስርጭት ችግር የፈታበት ዓመት እንደነበርም አስታውሰዋል ዋና ሥራ አስኪያጁ፡፡
ያለፈው በጀት ዓመት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ተሞክሮዎችን በመቅሰም ሚዲያው የበለጠ ተወዳደሪ እንዲሆን የተሠራበት ዓመት እንደነበር ያነሱት አቶ ሙሉቀን ለድርጅቱ ሠራተኞች በሚሰጡ የማነቃቂያና የእርስ በርስ ውይይቶች በሀገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ነፋስ መቋቋም እንድንችልና ሚዛናዊ እንድንሆን አግዞናልም ብለዋል፡፡
የግንባታ መዘግዬት፣ የተደራሽነት እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥ፣ ጥራትና የተለያዩ ጉዳዮች የድርጅቱ ችግሮች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡ ችግሮቹን በቀጣይ ለማስተካከልም ድርጅቱ በትኩረት እንደሚሠራ በማስገንዘብ፡፡
አብመድ ተደራሺነቱን ለማስፋትና ተወዳደሪ ለመሆን የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግለትም አቶ ሙሉቀን ለቋሚ ኮሚቴው ጠይቀዋል፡፡ በተለይም በድርጅቱ የሚስተዋለውን የመኪና እጥረትና የበጀት አመዳደብ ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት በአትኩሮት እንዲሠራበት ነው ቋሚ ኮሚቴውን የጠየቁት፡፡ ለድርጅቱ የሚሰጠው የገንዘብ ልክም በክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅና መገናኛ ብዙኃኑ አቅሙ የበለጠ ከፍ እንዲል መደገፍ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ ከሌሎች የክልል መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ጋር የነበረን ግንኙነት ያን ያክል የማያኮራ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ ድርጅቱ ሕዝብን ከሕዝብ፣ መንግሥትን ከመንግሥት ጋር የሚያጋጩ ሥራዎችን እንዳልሠራም አስታውቀዋል፡፡ ወደፊትም ሙያው በሚፈቅደው መስመር ሚዛናዊ የሆኑ ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
የሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂም የመገናኛ ብዙኃኑ የነበረውን ድክመትና ጥንቃሬም ለቋሚ ኮሚቴውና ለድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች አቅርበዋል፡፡ የዘገባ ተደራሽነትና ፍትሐዊነት፣ ጎጂ የሆኑ ልማዶችን ለማስቀረት ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን አጋር አካላት አድርጎ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ መሥራት፣ ሚዲያውን ለማዘመን ትልቅ ጥረት ማድረግ፣ ለውጡ ሕዝባዊ ሆኖ እንዲቀጥል፣ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የነበረው የፀጥታ ችግርን በተመለከተ የሠራቸው ሥራዎች እና በሌሎች ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የሠራቸው ሥራዎች የሚያስመሠግኑት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ብዙ መልካም ጎኖች እንዳሉት ያነሱት ወይዘሮ ሉባባ የሚሠሩ ሥራዎች ዘላቂነት አለመኖራቸው፣ ማራኪና ሳቢ በማድረግ በኩል ያለውን ክፍተት፣ የምርመራ ዘገባዎችን በደንብ አለመሥራትና ሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮች ማስተካከያ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ በተለይም ድርጅቱ ተወዳጅ የነበረባቸው የከተሞች መድረክ እና አንድ ለአንድ የተባሉ ዝግጅቶች መቋረጣቸው ለድርጅቱ መልካም እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ከኮሙዩንኬሽን የሚመጡ ዜናዎችን ተቀብሎ አለማስተናገድ፣ ከክልሉ ውጭ ላሉ የክልሉ ተወላጆች ሽፋን አለመስጠት እና በክልሉ የሚስታዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ተከታትሎ በማስፈታት በኩል ክፍተቶች እንዳሉበት አመላክተዋል፡፡ በቋሚ ኮሚቴው የቀረቡ ጥያቄዎች በድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከወረዳና ከዞን ኮሙዩኒኬሽን የሚመጡ ዜናዎች ከደረጃ በታች መሆንና በወቅቱ አለመድረስ እንዳይተላለፉ ምክንያት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮችም ለማስተካከል እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬም በተፈጠረው ሀገራዊና ክልላዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት አንዳንድ ዝግጅቶችን መያዝ እንዳስፈለገ ገልጸው አንዳንድ አካባቢዎች ለሚዲያው ያላቸው የተዛባ አመለካከት እንዲስተካከልና ሚዲያው የሕዝብ አገልጋይ መሆኑን እንዲያቁ መክረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂምም አብመድ ያለውን ጠንካራ ጎን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል፡፡ በድርጅቱ በኩል ለክልሉ መንግሥትና ለተከበረው ምክር ቤት እንዲቀርቡ የተነሱ ጥያቄዎችንም ለክልሉ ምክር ቤት በማቅረብ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴው እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን ብልሹ አሠራር በግልጽ በማውጣት በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ የሕዝብ ድምጽ ነው፡፡ ድርጅቱ አሁንም ነገም ቢሆን የሕዝብ ወገንተኝነቱን በማስቀጠል ለፍትሕና ለእኩልነት እየሠራ በምሥራቅ አፍሪካ ተመራጭ ሚዲያ ለመሆን እየታተረ ነው፡፡ በቅርቡም ለማኅበረሰቡ ካደረሰው አስተዋጽኦ አንጻር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጀው የጣና ሽልማት ተሸላሚ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ