የማክሰኞ ገበያ ሆስፒታል በጦርነቱ የከፋ ውድመት ቢደርስበትም ባለው አቅም ሁሉ አገልግሎት እየሰጠ ነው ተባለ፡፡

59
ባሕር ዳር:መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጠገዴ ወረዳ የሚገኘው የማክሰኞ ገበያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በጦርነቱ የከፋ ውድመት ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ሆስፒታሉ በሕክምና ቁሳቁስ፣ ባለሙያ እና መድኃኒት እጥረት ቢፈተንም ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ በቻለው አቅም ሁሉ ሕዝብን እያገለገለ ነው ተብሏል፡፡
በሰው ልጅ ሕይዎት፣ በሀገር ሃብት እና በሕዝብ ንብረት ላይ አስከፊ ውድመት ያደረሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ያለፉት ሦስት ዓመታት ግጭት እና ጦርነት ካጎሳቆላቸው ተቋማት መካከል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጠገዴ ወረዳ የሚገኘው የማክሰኞ ገበያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አንዱ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ከጦርነት ማግስት ጀምሮ በቻለው አቅም ሁሉ ወደ አገልግሎት ቢገባም የድህረ ጦርነት ድጋፉ ውድመቱን ታሳቢ ያደረገ ባለመሆኑ በቂ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ይላሉ አስተያየት ሰጭዎች፡፡
ወይዘሮ አትክልቲ የዓለምጌጥ የማክሰኞ ገበያ ነዋሪ ናቸው፡፡ የማክሰኞ ገበያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ነው የሚሉት ነዋሪዋ ነገር ግን በጦርነቱ የደረሰበት የከፋ ዘረፋ እና ውድመት አገልግሎቱ ተገልጋዮችን የሚያረካ አልሆነም ይላሉ፡፡ አቅም ያላቸው ታካሚዎች ወደ ቅራቅር እና ጎንደር እየሄዱ ይታከማሉ የሚሉት ወይዘሮ አትክልቲ የሆስፒታሉ አገልግሎት ሙሉ ባለመሆኑ ሕዝቡ አገልግሎቱ ላይ እምነት እንዳያሳድር ተጽዕኖ ፈጥሮበታል ነው ያሉት፡፡
ሆስፒታሉ ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ ወደ ሥራ በመግባት አገልግሎት በመስጠቱ ከነችግሮቹም ቢሆን ለብዙ ሰዎች ችግር ደርሷል ያሉት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ጀጀው ሃብቴ አስተያየት ሰጭዎቹ የሚያነሷቸው ችግሮች ግን ትክክል እና ተገቢዎች ናቸው ብለዋል ፡፡ እንደ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገለጻ ሆስፒታሉ በሕክምና ቁሳቁስ፣ ባለሙያ እና መድኃኒት እጥረት ቢፈተንም ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ በቻለው አቅም ሁሉ ሕዝብን እያገለገለ ነው ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ ከሚያስፈልጉት 170 ባለሙያዎች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑትን ብቻ ይዞ አገልግሎት እየሰጠ ነው ያሉት ዶክተር ጀጀው የባለሙያዎች ፍልሰት የተቋሙ ወቅታዊ ፈተና ሆኗል ይላሉ፡፡ ችግሩ ደግሞ ዞኑ በጀት ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የትርፍ ስዓት ክፍያ መክፈል አለመቻሉ ዋናው ችግር ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ለሆስፒታሉ በርካታ ባለሙያዎችን ቀጥሮ ነበር ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ የባለሙያዎችን ፍልሰት ግን መቋቋም አልቻለም ነው ያሉት፡፡ ሆስፒታሉ አምቡላንስ የሌለው መሆኑ አሁንም ድረስ መሰረታዊ ችግር ነው ተብሏል፡፡
ሆስፒታሉ በጦርነቱ የከፋ ውድመት የደረሰበት መሆኑን ተከትሎ በክልሉ ጤና ቢሮ እና በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ርብርብ በርካታ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደተደረገለት የነገሩን ደግሞ የጠገዴ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የኤች አይ ቪ እና ክትባት ኦፊሰር አቶ አልማው ብሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን የደረሰው ውድመት የከፋ በመሆኑ መልሶ ግንባታው ጎዳቱን የሚያካክስ ባለመሆኑ ችግሩ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ በችግር ውስጥም ሆኖ አገልግሎቱ አለመቋረጡ የክልሉ መንግሥት ጤና ቢሮ ድጋፍ ያልተለየው በመሆኑ ነው ያሉት አቶ አልማው አሁን ባለበት ችግር ውስጥ ሆኖ መቀጠል ስለለበት የሁሉንም አጋር አካላት የጋራ ርብርብ ይፈልጋል ብለዋል፡፡ ሆስፒታሉን ወደ ነበረበት አቅም ለመመለስ የጤና ሚንስቴርን እና አጋሮቹን ድጋፍ ስለሚፈልግ በችግሩ ልክ መነጋገር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ዘመናዊ የመስኖ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት የክልሉን አርሶ አደሮች የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው”
Next articleበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በቡሬ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ቋሚ ድጋፍ እያደረገ ነው።