“ዘመናዊ የመስኖ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት የክልሉን አርሶ አደሮች የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው”

129
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከ70 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ ለግብርና ምቹ የኾነ መሬት ያላት ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚታረሰው ከ14 ሚሊየን ሄክታር የተሻገረ እንዳልኾነ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ከ14 ሚሊየን ሄክታር በአልተሻገረ የእርሻ መሬት ለ120 ሚሊየን የሕዝብ መጋቢ፣ ለ80 ሚሊየን ሕዝብም የሥራ ዘርፍ ነው የኢትዮጵያ ግብርና።
በተለይ በግብርና ልማት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የአማራ ክልል ያለውን የመልማት ጸጋ ቢጠቀም አበርክቶው የላቀ እንደኾነ ነው የሚነገረው። ከተፈጥሮ ዝናብ የተንጠለጠለ የግብርና ሥራ ተሻግሮ ውኃን ለግብርና ሥራ በልኩ በመጠቀም የመስኖ ልማት ላይ መሥራት ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ ኾኗል።
የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ አየልኝ መሳፈንት እንደተናገሩት በአማራ ክልል 2 ነጥብ 2 ሚሊየን መሬት ለመስኖ ልማት ምቹ ነው።
እስከ አሁን እየተሠራበት ያለው ግን 10 ከመቶ ያልተሻገረ ነው።
ዘርፉ በበርካታ ችግሮች እየተፈተነ እንደኾነ የሚናገሩት ምክትል ቢሮ ኀላፊው የመስኖ ልማት ሥራ የአስተሳሰብ ለውጥን የሚሻ ነው ይላሉ።
በአዲስ የተቋቋመው መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ችግሮችን በጥናት ለይቶ እየሠራ እንደኾነ ነው የሚያስረዱት።
በክልሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች መጓተት፣ በታለመላቸው ልክ አገልግሎት አለመስጠት፣ የፕሮጀክቶቹ የዲዛይን ችግር፣ የተቋራጭ የመፈጸም አቅም ውስንነት፣ የአሰሪ መስሪያቤት የክትትልና ቁጥጥር ማነስና የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ችግር ለዘርፉ ፈተና እንደሆኑ በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።
መስሪያ ቤቱ በአዲስ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ቅድሚያ የመስኖ ፕሮጀክቶችን እንደየችግራቸው የማከም ሥራ ነው የተከናወነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶች በሚተገበሩበት አካባቢ ያለው አሥተዳደር፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለልማቱ ያለው የባለቤትነት ቁርጠኝነት ችግር ፈታኝ እንደነበር የሚናገሩት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በቀደመው የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ከዲዛይን እስከ ርክክብ የአሠራር ክፍተቶች እንደነበረ ነው የተናገሩት።
ቢሮው ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት “ዘመናዊ የመስኖ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት የክልሉን አርሶ አደሮች የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው” ተብሏል።
ክልሉ በዚህ ዓመት ከ1ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦ በተለያየ ምክንያት ያልተጠናቀቁ 279 ነባርና አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
123 ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢኾንም፣ የሲሚንቶ ችግር ፈታኝ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleእንሳሮ እና መርሀቤቴ ወረዳዎችን የሚያገናኘው የጀማ ድልድይ በመሰበሩ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን የመርሀቤቴ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next articleየማክሰኞ ገበያ ሆስፒታል በጦርነቱ የከፋ ውድመት ቢደርስበትም ባለው አቅም ሁሉ አገልግሎት እየሰጠ ነው ተባለ፡፡