
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የእንሳሮ እና መርሀቤቴ ወረዳዎችን የሚያገናኘው የጀማ ድልድይ ዛሬ በመሰበሩ መንገዱ ለተሽከርካሪ ዝግ ሆኗል። ይህ መንገድ ከአዲስ አበባ በሚዳ መርሀቤቴ በኩል እስከ ደሴ ድረስ የሚወስድ በአስፋልት ግንባታ ላይ የሚገኝ መንገድ ነው።
ከደብረ ብርሃን ወደ መርሀቤቴ ሚዳና ወረኢሉ ለመጓዝም የሚያገለግለው መንገድም ይህ መስመር ነው።
ዛሬ የመሰበር አደጋ የደረሰበት የጀማ ድልድይ ለረጅም ጊዜያት ጥገና ያልተደረገለትና በርካታ ተሽከርካሪዎችን ሲያሰተናግድ የቆየ ነው።
100 ሜትር ርዝመት ያለው የጀማ ድልድይ የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ የሆኑ ሁለት ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች በተመሳሳይ ጊዜ በድልድዩ ገብተው እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ነው የመሰበር አደጋ ደርሶበታል የተባለው።
የመርሀቤቴ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በቂነው ስለሺ ድልድዩ በአንድ ጊዜ አንድ ተሽከርካሪን ብቻ ማሳለፍ የሚችል ቢሆንም ባልተለመደ ሁኔታ ሁለቱ ተሽከርካሪዎች እንደጫኑ ወደ ድልድዩ በመግባታቸው የመሰበር አደጋው ተከስቷል ብለዋል።
ለጊዜው መንገዱ ለተሽከርካሪ ቢዘጋም መጭው የትንሣዔ በዓል በርካታ ተሽከርካሪዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ አስቸኳይ ጥገና እንዲሠራለት የማሳወቅ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
ጊዜያዊ ተለዋጭ መንገድ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:–ዮሐንስ ንጉስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!