“የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማስተካከል መንግሥት የማስፈጸም አቅሙን ተጠቅሞ የንግድ ሥርዓቱን መቆጣጠር እና ማስተካከል ይጠበቅበታል” የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አብዮት አልማው (ዶ.ር )

55
ባሕር ዳር:መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ያነጋገርናቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በተፈጠረው የዋጋ ንረት ምክንያት ህይዎታቸውን ለመምራት መቸገራቸውን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል። ወይዘሮ አስቴር ተፈራ በባህር ዳር ከተማ አዲሱ መናኸሪያ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። የቤት እመቤት እና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አስቴር ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት የትዳር አጋራቸው በሚያመጡት የወር ገቢ ነው። አሁን የተከሰተው የኑሮ ውድነት የቤተሰባቸውን ኑሮ እንደተፈታተነው ተናግረዋል፡፡ የወር ገቢያቸው እና ወጪያቸው ባለመመጣጠኑ ምክንያት የምግብ ፍላጎታቸውን ለመገደብ ተገደዋል፡፡ ወይዘሮ አስቴር ከሁለት ወር በፊት በ5 ሺህ ብር ሒሳብ የገዙት ጤፍ ዛሬ 7 ሺህ 6 መቶ ብር ኾኗል። የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመኾኑ የሚመለከተው አካል ተገቢውን እርምጅ እንዲወስድም ጠይቀዋል፡፡
በችርቻሮ ንግድ የሚተዳደረው እና ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ወጣት የዋጋ ንረቱ ገበያውን አቀዝቅዞበታል። ወጣቱ እንዳለው ለሽያጭ የሚያመጣቸውን የሸቀጥ ዕቃዎች በውድ ገዝቶ ለሽያጭ በሚያቀርብበት ጊዜ በሚከሰተው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ገቢያው እንደተቀዛቀዘበት ተናግሯል፡፡ የሸማቾችን የመግዛት አቅም የኑሮ ውድነቱ እየተፈታተነው በመምጣቱ ለቤት እና ለሱቅ ኪራይ ለመክፈል እንደተቸገረ ተናግሯል፡፡
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አብዮት አልማው የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣ መኾኑን ተናግረዋል። የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን እና ቋሚ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎችም አቅም እየፈተነ መኾኑን ዶክተር አብዮት አስረድተዋል፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የዋጋ ጭማሪው ጤነኛ ላለመኾኑ ማሳያዎች ፤ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣም፣ በሥርዓት የሚመራ የገበያ ሰንሰለት አለመኖር፣ አምራቹ እና ሸማቹ ፊት ለፊት ተገናኝተው የሚገበያዩበት ሥርዓት አለመኖር ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።
ዓለም አቀፋዊ ኹኔታዎች እና ግጭቶች በምርት እና በገበያው ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን የተናገሩት ዶክተር አብዮት ኅብረተሰቡ ኑሮውን በአስቸጋሪ ኹኔታ እንዲመራ ተገዷል፡፡ የተከሰተው የዋጋ አለመረጋጋት እና የዋጋ ንረት ዜጎች ከማምረት እንዲወጡ እና ሕገወጥነት እንዲስፋፋ ምክንያት እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡
የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማስተካከል መንግሥት የማስፈጸም አቅሙን ተጠቅሞ የንግድ ሥርዓቱን መቆጣጠር እና ማስተካከል ይጠበቅበታል ያሉት ዶክተር አብዮት ጥናትን መሠረት ያደረገ የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረብ፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ኀብረተሰቡን ከጎን በማሰለፍ የመረጃ ምንጭ እንዲኾን ማድረግ፣ የከተማ ግብርናን በበለጠ ማስፋፋት፣ ሸማቹ ቀጥታ ከአምራቹ ጋር የሚገናኝበትን የገበያ ሥርዓት ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በብዛት በማቋቋም መንግሥት በገበያ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሚጠበቅበት የተናገሩት ዶክተር አብዮት አምራቹ በቁርጠኝነት ወደ ሥራ እንዲገባ ተገቢ ድጋፍ ማድረግ እና ሂደቱን መከታተል የችግሩ መፍቻ ቁልፍ መኾኑን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፊቤላ የዘይት ፋብሪካ ባለፉት ጊዜያት ከ130 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
Next articleእንሳሮ እና መርሀቤቴ ወረዳዎችን የሚያገናኘው የጀማ ድልድይ በመሰበሩ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን የመርሀቤቴ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።