
ባሕርዳር: መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፊቤላ የዘይት ፋብሪካ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ችግር በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት እንዳደረገውም አስታውቋል፡፡
ፊቤላ የዘይት ፋብሪካ በኢትዮጵያ የዘይት አቅርቦት ችግርን ይቅርፋሉ ተብሎ ተስፋ ከተጣለባቸው ፋብሪካዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ የሀገሪቱን 60 በመቶ የዘይት አቅርቦት ይሸፍናል፡፡
የበላይነህ ክንዴ ግሪፕ የኮምዩንኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው ፋብሪካው በቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ማምረት አቅም አለው ነው ያሉት፡፡ ፋብሪካው በሀገር ደረጃ ትልቁ ፋብሪካ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ሀገራትም የተሻለ የሚባለው ፋብሪካ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የውጭ ምንዛሬ አለመገኘት የሚፈለገውን ያክል የፋብሪካውን ጥሬ እቃ ለመግዛት ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖበታል ነው ያሉት፡፡ የኤሌክትሪክ ኀይል ችግርም ሌላኛው የፋብሪካው ፈተና መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ፋብሪካው ስምንት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኀይል እንደሚያስፈልገው የተናገሩት ዳይሬክተሩ ለፋብሪካው የተሰጠው የኤልክትሪክ ኃይል አራት ሜጋ ዋት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የተሰጠው የኤሌክትሪክ ኀይል ከሚፈለገው በታች ከመሆኑም ባለፈ ከፍተኛ የሆነ የኀይል መቆራረጥ መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በቀን ከአምስት እስከ ስምንት ጊዜ ድረስ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንደሚያጋጥምም ተናግረዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት እና የምንዛሬ ችግር በሚፈለገው ልክ እንዳያመርት እንዳደረገውም አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት የውጭ ምንዛሬን ለመፍታት ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆዬ የተናገሩት ዳይሬክተሩ እንደ ሀገር ያጋጠመው የምንዛሬ ችግር ፈተና መሆኑን ነው ያነሱት፡፡ በመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ ፋብሪካው ካለው አቅም አንጻር በቂ አለመሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ካለችው ውስን የውጭ ምንዛሬ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡
የኀይል አቅርቦቱን ለመፍታት የተጀመሩት ሥራዎች በበቂ ሁኔታ እየሄዱ አለመሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው ጄኔሬተርን በመጠቀም እና ለውጭ ገቢያ በሚያቀርበው ዶላር ችግሮችን እየተቋቋመ በአንድ ዓመት ከሥምንት ወር ከ130 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ቢችል አሁን የተመረተው የስድስት ወር ምርት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ከዘይት ተረፈ ምርት ሳሙና እንዲመረት በማድረግ ከ30 በላይ የሚሆኑ ፋብሪካዎች እንዳይዘጉ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከፓልም ዘይት በተጨማሪ የሱፍ ዘይትን እያቀረበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ፊቤላ በቀጣይ ወራት የቅባት እህሎችን በመፍጨት አቅሙን እንደሚያሳድግም ገልጸዋል፡፡ የሳሙና እና የካርቶን ፋብሪካዎችን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ የአትክልት ቅቤ ላይ የራሱን ስም ይዞ ለመምጣት እየሠራ ነውም ብለዋል፡፡ ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆኑ የእርሻ ሥራዎችን እያስፋፋ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የቅባት እህል አምራች አርሶ አደሮች ከፋብሪካው ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዲኖራቸው እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፊቤላ ሰሊጥ ላይ እሴትን በመጨመር ለገበያ እንደሚያቀርብም ገልጸዋል፡፡ እሴት የተጨመረበት ሰሊጥን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገር እድገት አስተዋጽዖ ለማድረግ እየሠራ ነውም ብለዋል፡፡
ፊቤላ በቋሚና በኮንትራት ለ1 ሺህ 500 ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩንም ነው ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ የውጭ ምንዛሬ (ኤልሲ) ጉዳይ ባለመፈታቱ ያጋጠመውን የኤሌክትሪክ ሥራ በተፈለገው ልክ መሄድ አልቻለም ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬውን ጉዳይ ለማስፈታት ከብሔራዊ ባንክ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ችግሩ አልተፈታም ነው ያሉት፡፡
ከንግድ ባንክ ብድር መፈጸማቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የብር ችግር የለብንም፣ ከውጭ የሚመጣውን እቃ ለማስገባት ግን ኤል ሲ መከፈት አለበት ነው ያሉት፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ግፊት እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬው ችግር ከተፈታ ሥራው እንደሚፈጥንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!