ተለዋዋጭ የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ለመቋቋም የሥራ አጥነት ኢንሹራንስ ያስፈልጋል ተባለ።

89
ባሕር ዳር:መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን እና የዓለም ሥራ ድርጅት ከአማራ ክልል አሠሪዎች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በማኅበራዊ ዋስትና እና በሥራ አጥነት ኢንሹራንስ ዙሪያ በባሕርዳር ከተማ ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ውስብስብ እና ተለዋዋጭ የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ለመቋቋም የሥራ አጥነት ኢንሹራንስ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እና ኪሳራ በሚገጥማቸው ወቅት መልሰው እንዲያገግሙ እና በውስጣቸው የያዟቸው ሠራተኞች እንዳይበተኑ እና ኑሯቸው እንዳይናጋ የሥራ አጥነት ኢንሹራንስ ትልቅ ሚና ይጫዎታል ነው ያሉት።
በተለያዩ ምክንያቶች በአሠሪዎች ከሥራ ገበታቸው የሚሰናበቱ የግል ተቀጣሪዎች ኢኮኖሚያዊ ዋስትና እንዲያገኙም ያስችላል ተብሏል።
የሥራ አጥነት ኢንሹራንስ ሠራተኞች የደመወዝ ድጎማ እያገኙ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ወይም ደግሞ ወደ ሌላ ድርጅት ተዘዋውረው የሚሠሩበትን ዕድል የሚያመቻች ሥርዓት መኾኑንም ኢንጅነር ጌታሁን ተናግረዋል።
የሥራ አጥነት ኢንሹራንስ ተግባራዊ እንዲኾን ሠራተኞች እና አሠሪዎች የሚጠበቅባቸውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢንጅነር ጌታሁን ከጥቃቅንና አነስተኛ እስከ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችን ማኅበራዊ ዋስትና የሚጠብቅ ሁኔታ ማመቻቸት ይገባልም ብለዋል።
በግል ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች የጡረታ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የወጣው ዓዋጅ በትክክል ተግባራዊ እንዲኾን ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል አሠሪዎች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሱሌማን ኢብራሂም ፌዴሬሽኑ በክልሉ የሚገኙ አሠሪዎችን የሚወክል ነው ብለዋል። ፌዴሬሽኑ ከክልሉ የልማት ድርጅቶች እና ከግል ባለሃብቶች የተወጣጡ 54 አባላት እንዳሉት ጠቅሰዋል።
ፌዴሬሽኑ በአሠሪ እና ሠራተኛ ዙሪያ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ከመሄዳቸው በፊት ለማግባባት እና ለማስማማት በጋራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
አቶ ሱሌማን በፋብሪካዎች እና በሁሉም የሥራ አካባቢዎች ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል መልካም ግንኙነት መኖር አለበት ብለዋል። ይህ እንዲኾን ደግሞ በሁሉም ፋብሪካዎች የሠራተኛ ተወካዮች መኖር አለባቸው ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article12 ቢሊዮን ብር ያካበቱ ባለሃብቶች ወደ ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ገብተዋል።
Next articleስፖርት ዜና ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2015 ዓ.ም