
ባሕር ዳር:መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሃብት መጠን ያካበቱ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ እየገቡ መሆናቸውን የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አስታውቋል።
የኢንዱስትሪ መንደር ካላቸው የአማራ ክልል ከተሞች መካከል አንደኛዋ ቡሬ ናት። ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ በመሆን በርካታ ባለሃብቶችን እየሳበች ነው። ለከተማዋ እና ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለባለሃብቶች መዳረሻ ሆኗል።
የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሥራ አስኪያጅ ዳኛቸው አስረስ የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክን በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። አንድ ሺህ ሄክታሩን በሦስት ተከታታይ ምዕራፎች ለማልማት መታቀዱንም ነው የነገሩን። በ264 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና የመጀመሪያው ምዕራፍ በትግበራ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል። ሁለተኛ እና ሦስተኛው ምዕራፍ በቀጣይ ይከናወናል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ከ60 እስከ 100 የሚደርሱ ባለሃብቶችን እንደሚይዝም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በነበሩበት ፈተናዎች ወደ ፓርኩ መግባት የሚገባቸው ባለሃብቶች በታሰበው ፍጥነት አለመግባታቸውንም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል። ክልሉ በፈተና ውስጥም ሆኖ ከፍተኛ ድጋፍ ሲደረግለት መቆየቱንም ተናግረዋል። በመጀመሪያው ምዕራፍ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ባለሃብቶች መካከል 31 የሚሆኑ ባለሃብቶች ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኩ መግባታቸውንም አስታውቀዋል። ወደ ፓርኩ የገቡት ባለሃብቶችም 96 ሄክታር ቦታ ተረክበው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ተናግረዋል። የተረከቡት ቦታም መሠረተ ልማት የተሟላለት ነውም ብለዋል።
ወደ ፓርኩ የሚገቡ ባለሃብቶች የሚፈልጓቸውን ሁሉንም አገልግሎቶች በፓርኩ ውስጥ እንዲያገኙ ታስቦ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። ወደ ፓርኩ የገቡት 31 ባለሃብቶች 12 ቢሊዮን ብር ሃብት አካብተው የገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ወደ ፓርኩ የገቡ ፕሮጀክቶች ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የቡሬ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በልዩ ልዩ ሥራዎች ለተሠማሩ ከ3ሺህ በላይ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ከጀመረ ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳለውም ነግረውናል።
ሁለተኛው እና ሦስተኛው ምዕራፍ ተጠናቆ አንድ ሺህ ሄክታሩ ላይ ማልማት ሲቻል ደግሞ በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት። የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የአማራ ክልል ላቀደው የምጣኔ ሃብት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል። በፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ያሉ ቀሪ ቦታዎችን በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለባለሃብቶች እናስተላልፋለንም ብለዋል።
የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለቡሬ ከተማ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። አካባቢው ትርፍ አምራች መሆኑን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ የአካባቢውን ምጣኔ ሃብት እንደሚጨምርም ነው ያስረዱት። ፓርኩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!