በማኅበረሰቡ ተሳትፎ እየተገነባ ያለው ከገነትአቦ-ስሞኝ- ፈረስቤት መንገድ ግንባታ መቋረጡ አግባብ እንዳልኾነ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

123
ባሕር ዳር:መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከገነትአቦ-ስሞኝ- ፈረስቤት መንገድ ማኅበረሰቡ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ነበር እንዲገነባ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየው፡፡
መንገዱ 118 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ መንገዱ ሦስት ወረዳዎችን እና 6 ቀበሌዎችን ያገናኛል፡፡ 8 የአንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤቶችንም ተደራሽ ያደርጋል፡፡
መንገዱ በ2014 ዓ.ም በ440 ሺህ ብር ወጪ በላሊበላ ዲዛይን ማኅበር ዲዛይን ተሠርቶለት በ2015 ዓ.ም ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ መንገዱ መገንባት የተጀመረው በማኅበረሰቡ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ የማሽን ድጋፍ ነበር።
በምዕራብ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ የቀረበው ማሽን ከግማሽ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መጥረግ ባለመቻሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አንስተዋል።
የመንገድ ግንባታ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አለምነህ ዘሩ የአካባቢው ነዋሪ ለመንገዱ ግንባታ የተጠየቀውን ገንዘብ እያዋጣ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የምዕራብ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ መንገዱን ለማሠራት የሚያስችል ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
አቶ አለምነህ የብር ወንዝ ድልድይ ባለመገንባቱ በክረምት በርካታ ሰዎች በውኃ እየተወሰዱ መኾኑን አንስተዋል። የመንገዱ መገንባት የሦስቱን ወረዳዎች ሕዝብ በአንድ የመኖር ባሕል ያጠናክራል ብለዋል።
አቶ ድረስ ከበደ በበኩላቸው የመንገዱ አለመገንባት ነጋዴዎች ብዙ ርቀት እንዲጓዙ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን የግብርና ምርት ወደ ወረዳዋ ለማምጣት እና በወረዳው በብዛት የሚመረቱ ምርቶችን ለሌላው የማቅረብ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
የቋሪት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ መዝገቡ ውቤ መንገዱ ለወረዳዋ ነዋሪዎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለው ብለዋል፡፡
ሥራው በአካባቢው ተሳትፎ እና በዞኑ ድጋፍ ቢጀመርም የምዕራብ ጎጃም ዞን ያቀረበው ማሽን በመበላሸቱ መንገዱ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡
ወረዳው መንገዱን ከአማራ ልማት ማኅበር በሚደረግ ድጋፍ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ለመሥራት እየሞከረ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ነገር ግን በብር ወንዝ ላይ የተሠራው ድልድይ ጉዳት ሥላጋጠመው ድልድዩን ለመገንባት የመንግሥት ድጋፍ ማስፈለጉን አንስተዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ፈንታሁን መንግሥቴ በዞኑ ያለው የማሽን እጥረት መንገዱ በሚፈለገው ጊዜ መገንባት እንዳልተቻለ ነው ያስረዱት፡፡ የዞኑ አመራሮች ከመንገዱ አሰሪ ኮሚቴዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የአካባቢው ማኅበረሰብ ዶዘር እንዲያቀርብ እና ሌሎች የመሥሪያ ማሽኖችን ዞኑ ለማቅረብ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ፈንታሁን ድልድዩን ግን በዚህ ዓመት ለመሥራት ዕቅድ እንደሌለና ቀድመው ተራ የተያዘላቸው ሦስት ድልድዮች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ኢትዮጵያና ጣልያን ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መሥራት አለባቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን
Next article12 ቢሊዮን ብር ያካበቱ ባለሃብቶች ወደ ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ገብተዋል።