
ባሕር ዳር:መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያና ጣልያን ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ለአምባሳደሩ የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት፣የብሔራዊ ምክክር ሂደትና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ፣የመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ላይ ገለጻ ማድረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኢትዮጵያና ጣልያን የሁለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን የትብብር መስኮች ለረጅም ጊዜ የቆየና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸውም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ አገር ናት ብለዋል።
ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽና በባለ ብዙ መስክ ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!