ሴቶች ከሚያሳዩት የሥራ ቁርጠኝነት እና ውጤት አንፃር ሲታይ የውሳኔ ሰጭነት ቦታዎች ላይ ቁጥራቸው እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የብልጽግና ሴቶች ሊግ ገለጸ፡፡

49
አዲስ አበባ :መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ሴቶች ሊግ የ2015 ዓ.ም የዘጠኝ ወር አፈጻጸም እና ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን እየገመገመ ነው።
የዘጠኝ ወር ሪፖርቱን ያቀረቡት የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ወይዘሮ አሰለፍ ታደሰ በሪፖርታቸው እንደገለጹት በዘጠኝ ወሩ አፈጻጸም በተለያዩ ጊዚያት በተፈጠሩ መድረኮች ከ 12 ሚሊዮን በላይ ሴቶች የማንቃትና አቅም የማሳደግ ሥራ ተሠርቷል።
በውይይት መድረኮች ሴቶች ላይ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መለየታቸውን ያስረዱት ወይዘሮ አሰለፍ ከተገኙ ችግሮች መካከል የሴቶች የውሳኔ ሰጭነት ቁጥር ዝቅተኛ መሆን ከፍ ያለውን ደረጃ እንደሚይዝ አንስተዋል። ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያሉ የሴቶችን የአመራርነት ተሳትፎ ያለበትን ደረጃም አብራርተዋል።
በዚህ መሠረትም :-
👉የፌዴራል የሴቶች አመራርነት ተሳትፎ 18 በመቶ
👉የፓርላማ ተሳትፎ 42 በመቶ
👉የክልል አመራር ድርሻ 22 በመቶ
👉የዞን አመራር ድርሻ 28 በመቶ
👉የወረዳ የሴቶች የአመራር ድርሻ 27 በመቶ እንደሆነ ኀላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ አሰለፍ ሴቶች ከሚያሳዩት የሥራ ቁርጠኝነት እና ውጤት አንፃር የተሰማሩበት የኀላፊነት ደረጃቸው እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ወደፊት ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
➨የኑሮ ውድነት በተለዬ መልኩ ሴቶች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ፣
➨በሰላም እና መረጋጋት እጦት ሴቶች ቀጥታ ተጎጅ ስለመሆናቸው፣
➨የሴቶች ሥራ አጥነት ቁጥር ከፍተኛ መሆን እና ለተዛማጅ ችግሮች መጋለጥ፣
➨ሴቶች የቁጠባ በሕላቸው ከፍ ያለ ቢሆንም በተፈለገው መጠን የብድር ተጠቃሚ ሲሆኑ አለማዬት፣
➨የተሻለ የጤና አገልግሎት አለማግኘት፣
➨የተግባር ተኮር ትምህርት በበቂ ደረጃ ለሴቶች ተደራሽ አለመሆን፣
➨ለሕገ -ወጥ ስደት መዳረግ እና ከስደት ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጥ፣
➨ለተለያዩ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች የአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች የመጋለጥ፣
➨ለሚደርስባቸው ጥቃትም ተመጣጣኝ ቅጣት አለመኖር ችግሮች እንዳሉ ነው የተብራራው።
የሌማት ትሩፋት ሪፓርት ሌላኛው የመድረኩ አጀንዳ ሲሆን በዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሴቶች በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተዋቀሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሆነም ነው የተገለጸው። የሴቶች ኅብረት ሥራ ማኅበር በመፍጠር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ እንደሆነም አብራርተዋል ።
በሴቶች ላይ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ፣ማኅበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ነው በመድረኩ የተገለጸው።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከአትክልት እና ፍራፍሬ ሽያጭ በዓመት ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ የጠገዴ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
Next article“ኢትዮጵያና ጣልያን ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መሥራት አለባቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን