
ሁመራ :መጋቢት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጠገዴ ወረዳ በመስኖ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አሚኮ ያነጋገራቸው የዓለም ገነት ቀበሌ አርሶ አደሮች በቋሚ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት በዓመት ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፀሐይ ያለገደብ በተንሰራፋችበት በዚህ አካባቢ ፈጣሪ ለረድኤት እና በረከት፤ ለምርቱ እና ለከብቱ የካዛ ወንዝን ችሯቸዋል፡፡ ለዘመናት በጋ ከክረምት፤ ቀን ከሌሊት ሲፈስስ ውሎ ሲፈስስ የሚያድረው ወንዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በረከቱ እስከ መሀል ሀገር መድረስ ጀምሯል፡፡ የበርሃ ገነቷ ዓለም ገነት የካዛ ወንዝን ተጠቅማ ከቲማቲም እስከ ጥቅል ጎመን፤ ከሙዝ እስከ ሎሚ፤ ከፓፓያ እስከ ማንጎ ማከፋፈል ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል ብለውናል፡፡
አርሶ አደር ንጉሴ ግርማ በዓለም ገነት ቀበሌ የሂላብ ጎጥ አርሶ አደር ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእርሻ መሬታቸው የቅርብ ርቀት ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሰውን የካዛን ወንዝ ተጠቅመው ወደ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማት እንደተሰማሩ ነግረውናል፡፡ መጀመሪያ ቲማቲም እና ጥቅል ጎመን በመስኖ አለማ ነበር ያሉን አርሶ አደር ግርማ ጥቅሙ እየገባቸው ሲመጣ ግን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ቋሚ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት እንደተሸጋገሩ ነው የነገሩን፡፡
በወልቃይት እና ጠገዴ ወረዳዎች መካከል የሚገኘው የካዛ ወንዝ በርሃማውን ምድር እፎይታ ሰጥቶ አረስርሶታል ያሉን አርሶ አደሩ ለዓመታት ያላስተዋልነውን ጸጋ መጠቀም ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል ይላሉ፡፡ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በሚያለሙት የመስኖ ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ማሣ በዓመት እስከ 200 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙም አርሶ አደር ግርማ ተናግረዋል፡፡ “ከሚገኘው ገቢ በላይ በርሃማ በሆነችው ዓለም ገነት ቀበሌ የሂላብ ጎጥን ንጹህ አየር እና እፎይታ ማግኘት ሠላም ይሰጣል” ይላሉ፡፡
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በመስኖ ልማት የተሻለ አቅም ካላቸው ወረዳዎች መካከል ጠገዴ ወረዳ አንዱ ነው ያሉን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ አንጋው በላይ በወረዳው 1 ሺህ 638 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ 1 ሺህ 245 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል ብለውናል፡፡ በዓለም ገነት ቀበሌ ብቻ በመስኖ ቋሚ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የሚሳተፉ 150 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፡፡
በወረዳው ጉልበትን፣ ውኃን እና መሬትን አቀናጅቶ ማልማት ከተቻለ በርካታ አቅም ያላቸው አካባቢዎች አሉ ያሉት አቶ አንጋው በቀጣይ የመስኖ ልማት ሥራዎች የወረዳው የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸውም ብለውናል፡፡
አርሶ አደሮቹ ዓመቱን ሙሉ የሚያመርቱት ቋሚ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የአርሶ አደሮቹን ሕይዎት ከመለወጥ ባለፈ በከተሞች ያለውን የአቅርቦት ፍላጎት ማርካት የቻለ ነው ተብሏል፡፡ ተሞክሮውን ወስዶ ማስፋት የሁሉም ቀበሌዎች የግብርና ቤተሰብ ድርሻ እንደሆነም ቡድን መሪው ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!