
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላልና “ኦፕሬሽን” በተመለከተ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛነታቸውን እንዳረጋገጡ ታውቋል።
በዋሽንግተን የተወያዩት የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላልና “ኦፕሬሽን” በተመለከተ ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂ እና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛነታቸውን እንዳረጋገጡ የሚያመላክቱ መረጃዎች ወጥተዋል።
ሦስቱ የተፋሰሱ አባል ሀገራት በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ አራት ስብሰባዎችን ለማካሄድ ተግባብተዋል ነው የተባለው። በስብሰባዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዓለም ባንክ በታዛቢነት የሚሳተፉ ይሆናል።
ሀገራቱ እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 15 ቀን 2020 ድረስ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደተግባቡ፣ የስምምነቱን አፈፃፀም ለመገምገምና ለመደገፍም ሁለት ስብሰባዎችን በዋሽንግተን ለማከናወን ከስምምነት ላይ እንደደረሱ ተሰምቷል።
ሚኒስትሮቹ የአባይ ወንዝ ለሦስቱም ሀገራት ሕዝቦች ልማት አስፈላጊነቱን በማመን ድንበር ተሻጋሪ ትብብር ማድረግ እንደሚገባም ተወያይተዋል።