
ባሕር ዳር:መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሴቶች ሊግ በአዲስ አበባ ሦስት ክፍለ ከተሞች የተሠሩ የልማት ሥራዎችን አስጎብኝቷል።
ሥራው ሴቶችን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ የልማት ክንውን መሆኑ ተገልጿል።
በከተማ ደረጃ ከከተማ አሥተዳደር እስከ ግለሰብ ድረስ የተቀናጀ የልማት ቱሩፋቶች መከናወናቸው ነው የተብራራው።
በዶሮ እርባታ ፣በከብት ማድለብ ፣በበጎች እርባታ፣ በወተት ላሞች ፣በጓሮ አትክልት እና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።
በመድረኩ የብልጽግና ሴቶች ሊግ ፕሮዝዳንት ወይዘሮ ዛህራ ሑመድ ተገኝተው እንዳሉት “የልማት ሥራው ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) የወረደ እና ለሴቶች የተላለፈ እኛም ተቀብለን ተግባራዊ ያደረግነው ነው” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው “ዛሬ የተገናኘነው በሌማት ቱሩፋት በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የተፈጠረውን የልማት ንቅናቄ በተግባር በጋራ ውጤቱን ለማየት ያለመ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። የካ ክፍለ ከተማ፣ ለሚኩራ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የተሠሩ የልማት ትሩፋቶች የጉብኝቱ አካል ናቸው ብለዋል።
አዲስ አበባ የሁላችን ከተማ ፤የአንድነት መገለጫ ፤ሁሉን አስተባብራ የያዘች ፤የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቤትና የብልጽግና ተምሳሌት ከተማ ናት ብለዋል ኀላፊው።
ከተማዋ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች የተከናወኑባትና ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮዎች መሆን የሚችል ሥራ እንደተከናወነባትም አስረድተዋል። የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የእያንዳንዱ ዜጋ የምግብ ፍላጎት መረጋገጥ አለበት ነው ያሉት። በከተማዋ የእያንዳንዱ የቤት ጓሮና ግድግዳ አትክልት ማልማት በሚችል አግባብ እየተሠራ ስለመሆኑም ተመላክቷል።
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሃራ ኡሙድን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማና ክፍለ ከተሞች የብልጽግና ፓርቲ ኀላፊዎች ተገኝተዋል ።
ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን