
ባሕር ዳር:መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማኅበራት ግብጽ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ይዛ የቆየችውን አቋም ማስተካከል እንዳለባት ጠይቀዋል።
ከ30 በላይ የሚሆኑት ማኅበራቱ ጥያቄውን ያቀረቡት በትናንትናው ዕለት ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።
የግብጽ መንግሥት እና ሕዝብ ከያዙት የማደናቀፍ ተግባር ይልቅ በትብብር እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የጠየቁት ማኅበራቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተዛባ መረዳት አቁመው ግድቡ ለተፋሰሱ ሀገራት የሚያበረክተውን ጥቅም መረዳት አለባቸው ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ ለተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ለግብጽ እና ሱዳን በድርቅ ወቅት ውኃን በማቅረብ እንዲሁም በዝናብ ወቅት ደግሞ የጎርፍ አደጋን እና ደለልን በመከላከል የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጫቸው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለ4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት እየተዘጋጀች መሆኗን የጠቀሰው መግለጫው፣ 86 በመቶ የተፋሰሱን አስተዋፅኦ የምታበረክተው ሀገር ምንም ዓይነት የጥቅም ድርሻ እንዳይኖራት የሚያደረግ የግብጽ አቋም መስተካከል አንዳለበት አስገንዝበዋል።
የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውን ልዩ ትርጉም ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ እና ያለማንም እገዛ በራስ አቅም እየተገነባ ያለ ግድብ መሆኑን ጠቅሰው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከጨለማ ለመውጣት ተስፋ የሚያደርጉት ፕሮጀክት እንደሆነም ገልጸዋል።
የዳያስፖራ አባላቱ በአጠቃላይ ለግብጽ መንግሥት እና ሕዝብ ለግብጽ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ እንዲሁም ለዓረብ ሊግ አባል ሀገራት ግድቡን በተመለከተ ወደ ትብብር እና አጋርነት መንፈስ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!