
ባሕር ዳር:መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአገሪቱ በሚገኙ ስድስት ከተሞች በሚያከናውነው የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት 150 ሺህ አዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
እነዚህ አዲስ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በወላይታ ሶዶ፣ ሐረር፣ ሻሸመኔ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ከተሞች እያከናወነ በሚገኘው የመስመሮች መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት አማካኝነት ነው፡፡
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች የኤሌክትሪክ መስመር በአካባቢያቸው ተዘርግቶ ነገር ግን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ እንዲሁም ከተዘረጋው መሰረተ ልማት እስከ 2.5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኙትን የሚያካትት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በከተሞች ያለውን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝና ጥራት ያለው ለማድረግና የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችን መልሶ ለመገንባትና ለማሻሻል የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ ወጪ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከነዚህ መካከል የስድስቱ ከተሞች ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን እስካለፈው ጥር ወር ድረስ አፈፃፀሙ 74.35 በመቶ ደርሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ የኮንክሪት ምሰሶ ተከላ፣ የዝቅተኛና የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ፣ መስመር ላይ የሚገጠሙ መሳሪያዎችን ማሰር፣ ቀሪ ግብዓቶችን ወደ ግንባታ ቦታዎች ማጓጓዝ፣ የተመረቱ ግብዓቶች ፍተሻ ማከናወን የመሳሰሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
ፕሮጀክቱ በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!