በኢትዮጵያ 60 ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ ተከስቷል፤ ተደጋጋሚ የአውሮፕላን ብልሽት ደግሞ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል እንቅፋት ሆኗል፡፡

232

በተደጋጋሚ የመርጫ አውሮፕላን ብልሽት የእድገት ደረጃውን ጨርሶ እንቁላል ለመጣል በሚያስችለው ደረጃ በሰኔ ወር አጋማሽ 2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገባውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል እንቅፋት እንደሆነበት የግብርና ሚኒስቴር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

በትግራይ ክልል ሰባት ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል 10 ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ ወረዳዎች፣ በሶማሌ ክልል 12 ሁለት ወረዳዎች፣ በአፋር ክልል 21 ወረዳዎችና በድሬዳዋ መስተዳደር አንድ ወረዳ ላይ ከሰኔ 2011 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2012 ድርስ የበረሃ አንበጣው ተከስባቸዋል፡፡ የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ እንደቀጠለም በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ስላቶ ተናግረዋል፡፡
የመከላከል ሥራውን ፈታኝ ካደረጉት መካከል አንበጣው ያረፈባቸው አካባቢዎች በአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ አመች አለመሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከጎረቤት ሀገሮች ያልተቋረጠ የአንበጣ መንጋ ወደ ሁሉም ክልሎች መዛመት፣ የአየር ጸባዩ ለአንበጣው መራባት ምቹ መሆኑ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የወረዳና ቀበሌ አመራሮች ለችግሩ ትኩረት አለመስጠት ለመከላከል ሥራው እያጋጠሙ ካሉት ችግሮች መካከል መሆናቸውን አቶ ዘብዲዎስ ጠቅሰዋል፡፡

በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በአውሮፕላን፣ መኪናና በሰው ኃይል በመታገዝ 95 በመቶ የበረሃ አንበጣውን መከላከል እንደተቻለም አቶ ዘብዲዎስ አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከፍተኛ የመሬት ሽፋን ያለው አዳጊ አንበጣ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች እንደተፈለፈለና አንበጣው ባረፈባቸው ቦታዎች ሕዝብ የሰፈረ አለመሆኑ ችግሩን እንዳባበሰው አቶ ዘብዲዎስ ጠቅሰዋል፡፡

የበረሃ አንበጣውን በሙሉ አቅም ለመከላከል ከፌደራል 20 እንዲሁም ከክልሎች 17 መኪና መሠማራቱን የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ሳኒ ረዲ ገልጸዋል፡፡
ከፌደራል 26 እንዲሁም ከክልሎች 226 ባለሙያዎች ለዚሁ ሥራ መሠማራታቸውንም አቶ ሳኒ አስታውቀዋል፡፡

«‹ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚደርስልን የበረሃ አንበጣው ጉዳት ካደረስብን በኋላ ነው› እያለ የመረጠን ሕዝብ ይነግረናል፤ መሬት ላይ ያለውና እናንተ የምታቀርቡት ሪፖርት አይገናኛኝም» ሲሉ አንድ የቋሚ ኮሚቴው አባል ጥያቄ ማንሳታቸውም ታውቋል፡፡
የበረሃ አንበጣው ያደረሰውን የጉዳት መጠንና እየተሠራ ያለውን የመከላከል ሥራ ለመመልከት ከቋሚ ኮሚቴው የተውጣጣ ሁለት ቡድን ከዓርብ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ጀምሮ በአማራ፣ ትግራይ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ መስተዳድርና፣ ምዕራብ ሃረርጌ ዞን ላይ የመስክ ምልከታ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

Previous articleርዕሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ እና በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር በክልሉ በተመድ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ድጋፍ የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ ውይይት አደረጉ፡፡
Next articleሀገራቱ የህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላል በተመለከተ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛነታቸውን አረጋገጡ።