
ባሕርዳር: መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ከያሶ- ጋሌሳ-ድባጤ-ቻግኒ ያለው መንገድ የአማራ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎችን በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚያስተሳስር ረጅም እድሜ ያስቆጠረ መንገድ ነው፡፡መንገዱ ከሁለቱ ክልሎች አልፎ ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው የከበሩ ማዕድናት የሚተላለፍበት መንገድም ነው፡፡ለአብነትም እብነ በረድ ፣ ወርቅ ፣የድንጋይ ከሰል እና መሰል ማዕድናት ዓመቱን ሙሉ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይጓጓዝበታል፡፡
መንገዱ ካለው የትራፊክ ፍሰትና እንቅስቃሴ አንፃር ክረምት በገባ ቁጥር ብልሽት ስለሚያጋጥመው ማኅበረሰቡ በትራንስፖርት እጦት ሲቸገር ቆይቷል፡፡ አልፎ ተርፎም ወደ ህክምና ማዕከል ደርሰው መዳን የሚችሉ እናቶች እና ሕፃናት ሕይወታቸው በመንገድ ላይ ያልፋል፡፡ ካለው ችግር አንጻር የአካባቢው ነዋሪዎች መንገዱ ወደ አስፋልት ይቀየርልን ጥያቄ ለፌዴራሉ መንግሥት ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
መንግሥትም የኅበረተሰቡን ችግር በመረዳት እና መንገዱ እየሰጠ ያለውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ግምት ውስጥ በማስገባት ከቻግኒ-ድባጤ-ጋሌሳ-ያሶ ድረስ 117 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን መንገድ ወደ አስፋልት እንዲቀየር ተወስኖ በጀት ተይዞለት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ሥራው ሲከናወን ቆይተዋል፡፡
ከያሶ-ጋሌሳ-ድባጤ-ቻግኒ 117 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ በፌዴራል መንግሥት ሁለት ቢሊዮን 732 ሚሊዮን 402 ሺህ 166 ብር በጀት ተይዞለት በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ መንገድ መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ያሶ-ጋሌሳ-ድባጤ እስከ ቻግኒ ድረስ ያለውን የአስፋልት መንገድ በቻይናው ው ዩ ኮ ኤልቲዲ ተቋራጭ እየተከናወነ ቢሆንም ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ተቋራጩ በሎት ሁለት የተመደበውን ከድባጤ እስከ ቻግኒ ድረስ ያለውን 40 ኪሎ ሜትር መንገድ ብቻ ለመሥራት ተገድዷል፡፡
የመንገድ ሥራው ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ድልበድል ዘበኛው እንዳሉት መንገዱ አሁን ላይ ከአጠቃላይ ሥራው 16 በመቶ ደርሷል። ከድባጤ- ቻግኒ ድረስ ያለው 40 ኪሎ ሜትር መንገድ የቅድመ አስፓልት ሥራዎቹ ተጠናቅቀዋል ነው ያሉት፡፡
እንደ ተቋጣጣሪ መሐንዲስ ድልበድል ማብራሪያ የያሶ-ጋሌሳ-ድባጤ-ቻግኒ የአስፋልት መንገድ መገንባት ከሁለቱ ክልሎች አልፎ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ በመሆን የሚያገለግል መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክት ሥራው መጀመር ለአካባቢው ማኅበረሰብ የፈጠረው ደስታ ከፍተኛ ነው ያሉት መሐንድስ ድልበድል ማኅበረሰቡ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ እስከ አሁን ሥራው ላይ ምንም አይነት መስተጓጎል እንዳልፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ ከቻግኒ-ድባጢ ያለው የአስፋልት መንገድ ሥራው ቀጣይ ዓመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ብለዋል፡፡
የጓንጓ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳሉት የተጀመረው የአስፋልት መንገድ የበርካታ ዓመታት የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ነው። በምንም ምክንያት እንዳይስተጓጎል በከፍተኛ ሁኔታ ክትትል እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ሰላም የተረጋጋ እንዲሆን በተለይም ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
መንገዱን ወደ አስፋልት ለመቀየር ሥራ መጀመሩ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በመንገድ ችግር ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት የሚያስቀርላቸው መሆኑን በመንገድ ፕሮጀክቱ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣት መለሰ ገድፈው እና ወጣት ብርቱካን ዳኛው ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ መንገዱ ባይጠናቀቅም ለትራንስፖርት ምቹ በመሆኑ ወደ ቻግኒ እና ድባጢ ያለምንም ችግር እና እንግልት የትራንስፖርት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸው እንዳስደሰታቸው የአካባቢው ነዋሪ አቶ አየነው ታደለ እና ምናየሁ ጥላሁን ነግረውናል፡፡ ነዋሪዎቹ ለቀጣይም መንገዱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እስከሚበቃ ከካሳ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ማኅበረሰቡ እና ተቋራጮች በጋራ ተቀናጅተው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰሎሞን ስንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!