
ባሕር ዳር:መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለቀጣዮቹ የትንሳዔ እና ዒድ ዓልፈጥር በዓላት ከ13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስከረም ባህሩ እንደገለጹት ለመጪዎቹ በዓላት የመሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም ከሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አሥተዳደሮች እና የፌዴራል ተቋማት ጋር የጋራ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም በበዓላት ወቅት ይበልጥ ተፈላጊ ለሆኑ እና እጥረት በሚከሰትባቸው ምርቶች ላይ በየደረጃው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ከምግብ ዘይት አቅርቦት ጋር ተያይዞ በመንግሥት ከውጭ የሚገባ እና በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች የተመረተ ዘይትን ለበዓላቱ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ከፊቤላ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እና ከሸሙ ደግሞ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለክልሎች መደልደሉን ሥራ አስፈጻሚዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኘውን የምግብ ዘይትም አከፋፋዮች በፍጥነት አንስተው ከበዓላቱ በፊት ለክልሎች ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡
በሌላ በኩል በንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከዚህ በፊት ከውጭ ገብቶ ያልተሰራጨ 1 ሚሊዮን ሊትር ዘይት መኖሩን ጠቁመው አሁን ላይም 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በመጓጓዝ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይም ከኮርፖሬሽኑ 6 ሚሊዮን ሊትር እንዲሁም ከፊቤላና ሸሙ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በድምሩ ከ13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ለበዓላቱ ለገበያ ለማቅረብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የዘይት ምርቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብተረሰቡ ተደራሽ እንዲሆንም በየደረጀው በሚገኙ የመንግሥት አካላት አስፈላጊው ቁጥጥር ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!